በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በትናንትናው እለት ውይይት ተካሂዷል
የህዳሴው ግድብ የመጀመሪያ ዓመት የዉሃ ሙሌት ተጠናቀቀ
በወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበርና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ መሪነት በቪዲዮ ኮንፈረንስ በተካሄደው ስብሰባ ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፣ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ እና የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ተሳትፈዋል።
በተጨማሪም የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ መሃመትን ጨምሮ የቢሮው አባላት የሆኑት የኬንያ፣ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና የማሊ ሀገራት መሪዎች እና ተወካዮችም በውይይቱ ታድመዋል።
በውይይቱ በአበይት ጉዳዮች ላይ ስምምነት መደረሱን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ከውይይቱ በኋላ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ኢትዮጵያ በግብጽና በሱዳን ላይ ጉልህ ጉዳት ሳታደርስ የዓባይን ዉሃ በፍትሀዊ እና ምክንያታዊ መንገድ ለመጠቀም ያላትን አቋም እንደምትቀጥል አስታውቃለች፡፡
ኢትዮጵያ ፣ ሱዳን እና ግብጽ በግድቡ ውሃ አሞላል ዙሪያ ቴክኒካዊ ውይይቶችን በአፍሪካ ህብረት በኩል ቀጥሎ ለማካሄድ የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸውም ተገልጿል፡፡
ውይይቱን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ፣ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት በሚያጠናክር መልኩ በፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ መሪነት በግድቡ ዙሪያ ፍሬያማ ዉይይት መካሄዱን ገልጸዋል፡፡ በግድቡ ውሃ አሞላል ዙሪያ ቴክኒካዊ ውይይቶችን ቀጥሎ ለማካሄድ የጋራ መግባባት ላይ ለደረሱት የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ እና ለግብጽ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲም አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት በነበረው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት በመጀመሪያው ዓመት ግድቡን ለመሙላት የታቀደው የዉሃ ሙሌት መሳካቱም በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡ ሙሌቱ ተጠናቅቆ የወንዙ ዉሃ በግድቡ አናት ላይ መፍሰስ መጀመሩም ነው የተገለጸው፡፡ ይሁን እንጂ ግድቡ ከወቅታዊው ከፍተኛ የዝናብ መጠን ጋር በተያያዘ ከመሞላቱ ባለፈ በመንግስት ዉሳኔ ቦዮች ተዘግተው ስለመሞላቱ የተባለ ነገር የለም፡፡
ከቀናት በፊት የዉሃ ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ በሰጡት መግለጫ በከፍተኛ ዝናብ ምክንያት ግድቡ ዉሃ መያዝ መጀመሩን ገልጸው የመጀመሪያው ዓመት የዉሃ ሙሌት ተሳክቶ በቅርቡ ዉሀው በግድቡ አናት ላይ መፍሰስ እንደሚጀምር መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ሚኒስትሩ የግድቡ የዉሃ ሙሌት እና ግንባታው ጎን ለጎን የሚካሄዱ መሆናቸውን እና በክረምቱ ዝናብ ተፈጥሯዊ ሂደቱን ጠብቆ ሙሌቱ እየተካሄደ ስለመሆኑ በሳተላይት የወጡ ምስሎች የሚያሳዩት መረጃ ትክክለኛ መሆኑን በወቅቱ ተናግረዋል፡፡
የኢፌዴሪ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው የትናንቱም ዉይይት ተከትሎ በትዊተራቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ “ዓባይ ወንዝ…ወንዝም ሀይቅም ሆነ” በማለት የግድቡን የዉሃ ሙሌት አብስረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በመጀመሪያው ዓመት 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ዉሃ ለመሙላት አቅዳ ስትሰራ የነበረ ሲሆን ይህም የግድቡን የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ስራ በሁለት ተርባይኖች ለመፈተሽ ያስችላል ነው የተባለው፡፡
አሁን ላይ የግድቡ የግንባታ ከፍታ ከባህር ጠለል በላይ 560 ሜትር (ከመሰረቱ 40 ሜ.) ከፍታ ላይ የደረሰ ሲሆን የግንባታ ሂደቱም እስከ 640 ሜ. ከፍታ (ከመሰረቱ 140 ሜ.) ጎን ለጎን እንደሚቀጥል ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ባለፈው ሳምንት ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ “ለቀጣይ ልማቴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው” የምትለውን ይህን ግድብ ግብጽ በስጋት ትመለከተዋለች፡፡ ግብጽ “ግድቡ ከዓባይ ወንዝ ላይ የማገኘውን የዉሃ መጠን ይቀንስብኛል” የሚል መከራከሪያ ታነሳለች፡፡