የኢትዮጵያ ህገ መንግስት "መደበኛ ባልሆነ መንገድ" መሻሻል መጀመሩን ሰላም ሚንስቴር ተናገረ
“ሕገ መንግሥቱ ለውጥ ያስፈልገው ይሆን? ከኾነስ የትኞቹ ድንጋጌዎች” በሚል የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲቲዩት ጥናት አካሂዷል
ህገ መንግስቱን በሚመለከት ካሉ ሦስት ምልከታዎች ሁሉንም ባካተተ መልኩ መሻሻል የሚለው ሚዛን ይደፋል ተብሏል
የኢትዮጵያ ህገ መንግስት "መደበኛ ባልሆነ መንገድ" መሻሻል መጀመሩን የሰላም ሚንስትር ዴኤታ ስዩም መስፍን (ዶ/ር) ተናግረዋል።
የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ለውጥ ያስፈልገው ይሆን? ከሆነስ የትኞቹ ድንጋጌዎች በሚል የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲቲዩት ጥናት አካሂዷል።
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲቲዩት ባደረገው ጥናት ማብሰሪያ ላይ የሰላም ሚንስትር ዴኤታ ስዩም መስፍን (ዶ/ር) ምንም እንኳን ህገ መንግስቱ አልተሻሻለም ይባል እንጂ የተለያዩ አንቀጾች በአዋጅና በትርጉም እንዲሁም በሌላ መንገድ ተሻሽለዋል ብለዋል።
ህገ መንግስቱ በመደበኛም ይሁን በኢ-መደበኛ መንገድ እንደሚሻሻል የጠቀሱት ሚንስትር ዴኤታው፤ ህገ መንግስቱ ሙሉ ሊሆን እንደማይችል ተናግረዋል።
የፌዴራሉ አባል ክልሎችን የሚደነግገው አንቀጽ 47 ስለመሻሻሉ ጠቅሰዋል።
የፌዴራልና የክልል የጋራ ገቢዎች የሚወስነው አንቀጽ 58 እንዲሁም መሬት አስተዳደርን የሚደነግገው አንቀጽ 89 እና ሌሎች አንቀጾች መሻሻላቸውን ስዩም መስፍን (ዶ/ር) አንስተዋል።
ህገ መንግስቱን በሚመለከት ሦስት አይነት ምልከታዎች አሉ ያሉት ሚንስትር ዴኤታው፤ "ህገ መንግስቱ ረብ የለውም፣ በፍጹም መነካት የለበትም እንዲሁም ሁሉንም ባካተተ መልኩ ይሻሻል" የሚሉ ለየቅል ሀሳቦች መኖሯቸውን ተናግረዋል ሲል አሚኮ ዘግቧል።
ሚንስትር ዴኤታው "ጠቃሚው ሀሳብ ሁሉንም ባካተተ መልኩ ይሻሻል" የሚለው እንደሆነ አንስተዋል።
ህገ መንግስቱን ማሻሻል እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ያነሱት ስዩም መስፍን (ዶ/ር)፤ የማይሻሻል ከሆነ ጥያቄ የሚያነሱ አካላት ሙሉ በሙሉ በኃይል የመቀየር እንቅስቃሴ እና ፍላጎት ሊያሳዩ እንደሚችሉ ገልጸዋል።
በሀገሪቱ ያሉ የግጭትና የአለመግባባት ጉዳዮችን በቀላሉ ለመፍታት እንዲያስችል ሁሉንም ያማከለ ሀሳብ ይዞ ህገ መንግስቱን ማሻሻያ መልካም እንደሆነም አሳስበዋል።
በፕሮግራሙ የመነሻ ሃሳብ ያቀረቡት የኢፌዴሪ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር በየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር) ሕገ መንግሥቱ ከተረቀቀበት ጊዜ አንስቶ የክርክር ምንጭ መኾኑን ጠቅሰዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች ለሚፈጠሩ ችግሮች፣ መፈናቀሎች እና ብሔር ተኮር ግጭቶች ሕገ መንግሥቱ መሰረታዊ ድጋፍ ይሰጣል የሚሉ ሃሳቦች ይደመጣሉ፡፡ በሌላ በኩል የማንነት መሰረት ነው የሚሉም አሉ፡፡