ባንኩ “በህገ ወጥ የውጭ ሀገራት ገንዝብ ምንዛሬ ላይ የተሰማሩ አካላትን ለጠቆመም እስከ 25 ሺህ ብር ወረታ እከፍላሁ” አለ
በጥቁር ገበያ ላይ ተሰማርተው የነበሩ 391 ሰዎች የባንክ ሂሳብ እንዲዘጋ መደረጉን ብሄራዊ ባንክ አስታወቀ
ብሄራዊ ባንክ ከሚፈቅደው መጠን በላይ ገንዘብ ከባንክ ውጪ ያስቀመጠና ወርቅ ያከማቸ ግለሰብን ለጠቆመም ወረታአ እከፍላለሁ ብሏል
በህገ ወጥ የውጭ ሀገራት ገንዝብ ምንዛሬ ላይ የተሰማሩ አካላትን ለጠቆመም እስከ 25 ሺህ ብር ወረታ እንደሚከፍል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባክ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ በዛሬው እለት፤ የጥቁር ገበያ ቁጥጥርና አስተዳደራዊ እርምጃ፤የዋጋ ግሽበትና ህገወጥ የውጭ አገራት ገንዘብ ግብይትን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ፤ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያ በማድረግ በኢትዮጵያ ውጤት እየተመዘገ ቢገኝም የዋጋ ግሽበትና ምርታማነትን ከማሳደግ የንግድ ስርዓቱን ከማዘመን አንፃር ውስንነት እንዳለ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ህገወጥ የውጭ አገራት ገንዘብ ምንዛሬም ለዋጋ ግሽበትና ንግድ ስርዓቱ የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ህገወጥ የውጭ አገራት የገንዘብ ምንዛሬ የሃዋላ አገልግሎት ስራ የሚሰሩ አካላት ላይ አስተዳራዊ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የውጭ አገራት ገንዘብን በጥቁር ገበያ ህገወጥ የምንዛሬ ሃዋላ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ 391 ሰዎች የባንክ ሂሳባቸው እንዲዘጋ መደረጉንም አስታውቀዋል።
የግለሰቦቹን ስም ዝርዝር ለፍትህ ሚኒስቴር በመላክም ህጋዊ ምርመራ እንዲደረግባቸው እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በህገወጥ የሃዋላ የውጭ አገራት ገንዝብ ምንዛሪ ላይ የተሰማሩ አካላትን ለጠቆመም እስከ 25 ሺህ ብር ወረታ እንደሚከፈልም ጠቁመዋል።
ዶክተር ይናገር ደሴ፤ አክለውም፤ ገንዘብ በባንክ መቀመጥ እንዳለበትና የግብይት ስርዓትም በባንክ ማካሄድ እንዳበት በመግለጫቸው አንስተዋል።
ኢትዮጵያዊያንም በግለሰብ ደረጃ ከ100 ሺህ ብር በላይ ለድርጅቶች ደግሞ ከ200 ሺህ ብር በላይ ቤት ውስጥ ማስቀመጥ የተከለከለ መሆኑን መገንዘብ እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።
መመሪያው ከሚፈቅደው የገንዘብ መጠን በላይ አስቀምጦ የተገኘን አካል የጠቆመ ግለሰብ 15 በመቶ የወረታ ክፍያ እንደሚፈጸም ገልጸዋል።
ወርቅን በህገወጥ መልኩ ቤት ውስጥ አከማችቶ እንደማይቻልና በህገወጥ መልኩ ወርቅን ያከማቸ ግለሰብ ለጠቆመም ግለሰብ ባንኩ በወቅቱ ባለው ግብይት የ15 በመቶ ወረታ ይከፈለዋል ብለዋል።
በህገወጥ ገንዘብ ህትመት የተሰማሩ አካላትን ያጋለጠም ከ20 ሺህ እስከ 200 ሺህ ብር ወረታ እንደሚከፈለው አረጋግጠዋል።
ጠቋሚዎችም ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።