በወለጋ የመከላከያ ዩኒፎርም ለብሶ ከሟቾች ጋር ፎቶ የተነሳ የለም፤ የተቀነባበረ ነው - መከላከያ
ድርጊቱ በንፁሃን ደም የሚነግዱ ሴረኞች ተግባር ነው ብሏል የመከላከያ ሚኒስቴር
ህዝባዊ ሰራዊቱን ጥላሸት ለመቀባት የተደረገው ሙከራ ቀን ከሌሊት የሚሠሩ የኢትዮጵያ ጠላቶች ሴራ መሆኑንም ገልጿል
ከሰሞኑ በወለጋ ከተከሠተው የንፁሃን ግድያ ጋር ተያይዞ የመከላከያ ወታደራዊ ዩኒፎርም የለበሰና ራሱን በራሱ (ሰልፊ) የሚነሳ ወታደር ምስል በማህበራዊ ሚዲያ ተሰራጭቷል።
ምስሉ የመከላከያ ስራዊት ልብስ የለበሰ ወጣት የተገደሉ ዜጎች ጋር ራሱን ፎቶ ሲያነሳ ያሳያል።
የመከላከያ ሚኒስቴር ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ግን ምስሉ ሆን ተብሎ የተቀነባበረና በንፁሃን ደም የሚነግዱ የሴረኞች ተግባር መሆኑን ገልጿል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ተልዕኮውን እና የቆመለትን ዓለማ ጠንቅቆ እንደሚያውቅ የገለጸው ሚኒስቴሩ፥ ሠራዊቱ በህዝባዊ ወገንተኝነቱ ተምሳሌት የሆነ ሃይል መሆኑም ይታወቃል ብሏል።
ይሁን እንጂ የዜጎች በሠላም ወጥቶ መግባት የሚጎረብጣቸው የንፁሃን ሞት ነጋዴዎች በሰራዊቱም ሆነ በህዝቡ ላይ በሴራ የተጎነጎነ ተንኮል መሸረባቸውን ቀጥለዋል ነው ያለው መግለጫው፡፡
ከሠሞኑ በወለጋ ከተከሠተው የንፁሃን ግድያ ጋር ተያይዞ ተቀናብሮ የተለቀቀው የመከላከያ ወታደራዊ ዩኒፎርም የለበሰ ሰውን የሚያሳይ ምስልም መከላከያ ሠራዊቱ ላይ ጥላሸት የመቀባት ዘመቻ መከፈቱን እንደሚያሳይ መግለጫው አመላክቷል።
የዚህ ተግባር ዋነኛ አላማም “መከላከያ ሠራዊቱ ሀገሩንና ህዝቡን በመታደግ የተጎናፀፈውን ክብር፣ ታማኝነት እና ጀግንነት ለመሸርሸር ነው” ብሏል።
ህዝብን በብሄር ስም በማጋጨትና የአብሮነቱ መረብ እንዲበጠስም ሆን ተብሎ ታስቦበት የተሰራው ምስል መሰራጨቱን ነው የመከላከያ ሚኒስቴር መግለጫ የሚያመላክተው።
በሠው ደም የሚነግዱ የጥላቻ እና የግጭት ነጋዴዎች ሁለት እና ከዚያ በላይ ፎቶዎችን አቀነባብረው የመከላከያ ሠራዊትን ስም ለማጠልሸት የተደረገው ሙከራ ኢትዮጵያን የጦር አውድማ ለማድረግ የሚሠሩ ጠላቶች ሴራ መሆኑን መገንዘብ ይገባልም ብሏል መከላከያ።