መንግስት በወለጋ የሚፈጸመውን የማያባራ ግድያ ለምን ማስቆም አልቻለም?
ሸኔን በተፈለገው ፍጥነት ማስቆም ያልተቻለው መንግስት ወደ ሰሜን አተኩሮ ስለነበር ነው ብሏል መንግስት
ኢስመኮ ኦሮሚያን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች የሚፈጸሙ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግድያዎችን ለማስቆም የፖለቲካ መፍትሄ ያስፈልጋል ብሏል
በኦሮሚያ ክልል በሚገኙት አራት ዞኖች ማለትም በምእራብ ወለጋ፣በምስራቅ ወለጋ፣ በሆሮ ጉድሩ ወለጋ እና በቄለም ወለጋ ዞኖች የሚፈጸመው የንጹሃን ሰዎች ግድያ እና መፈናቀል ሊቆም አልቻለም፡፡
የችግሩ ሰለባ የሆኑ ነዋሪዎች ማንነታቸውን መሰረት ያደረገ ጥቃት እየተፈጸመባቸው እንደሆነ በተጋጋሚ ይናገራሉ፡፡
የሚፈጸሙጽን ግድያ እና ማፈናቀል በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ) መግለጫ ሲያወጣ ቆይቷል፡፡ ኢሰመኮ የሚፈጸሙት ግድያዎች እና ማፈናቀሎች ማንነትን መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን የገለጸበት መግለጫም ነበር፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ ለሚፈጸመው የጅምላ ግድያ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰውን እና በአሸባሪነት የተፈረጀውን ኦነግ ሸኔን ይከሳል፡፡ መንግስት ክሱን ቀጥሏል፤ግድያውም አልቆመም፡፡
- “የጸጥታ አካላት ጥቃቱ ወደተፈጸመበት አካባቢ ተሠማርተው እርምጃ እየወሰዱ ነው”-ጠ/ሚ ዐቢይ
- በምስራቅ ወለጋ በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት ከ150 በላይ ነዋሪዎች መገደላቸውን ተረድቻለው- ኢሰመኮ
በወለጋ ዞኖች የተፈጸሙ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግድያዎች
ምእራብ ወለጋ ዞን አስቃቂ የሚባል የንጹሃን ግድያ እና መፈናቀል በማስተናገድ ቀደሚ ነው፡፡ መንግስት ለተፈጸመው ግድያ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎችን ተጠያቂ አድርጓል፡፡
በጥቅምት 2013ዓ.ም በዞኑ የጉሊሶ ወረዳ፣ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ሽብር ነው ባለው ጥቃት 32 ሰዎች ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ መገደላቸውን ማረጋገጡ ይታወሳል፡፡
ኢሰመኮ የሟቾችን ቁጥር ወደ 54 ከፍ ያደርገዋል፡፡ኢስመኮ አገኘሁት ባለው ሪፖርት የተፈጸመው ግድያ “በሶስት ቀበሌዎች ላይ በሚኖሩ አማራዎች ላይ ያነጣጠረ” ነበር፤ ሊወገዝ እንደሚገባም ገልጾ ነበር፡፡
የአማራ ብልጽግና ፓርቲም ባወጣው መግለጫ የጉሊሶው ግድያ ማንነት ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ማረጋገጡን መግለጹ ይታወሳል፡፡ ጭካኔ በተሞላበት ድርጊት የአማራ ህዝብና ፓርቲው ክፉኛ ማዘኑን የጠቀሰው መግለጫው፤ድርጊቱ ሊወገዝና አጥፊዎች ለህግ ቀርበው ተጠያዊ መሆን አለባቸው ብሎም ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም ዘግናኝ ነው የተባለውን የጉሊሶ ግድያ በወቅቱ አውግዘዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጉሊሶ ወረዳ በተፈጸመው ጥቃት የተሰማቸውን ሀዘን በገለጹበት መግለጫቸው ፣ “በኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ ባለው ማንነትን መሠረት ባደረገው ጥቃት እጅግ ማዘኔን እገልጻለሁ” ማለታቸው ይታወሳለል፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጸጥታ አካላት ጥቃቱ ወደ ተፈጸመበት አካባቢ ተሰማርተው እርምጃ እየወሰዱ መሆናቸውን ገልጸው ነበር፡፡
በጉሊሶ የነበረውን ጥቃት ነዋሪዎች፣ኢሰመኮ፣የአማራ ብልጽግና ፓርቲ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እንደነበር ገልጸዋል፡፡
በዚሁ በምእራብ ወለጋ ዞን ባቦ ጋምቤል ወረዳ በተፈጸመ ጥቃት የ28 ሰዎች መገደላቸውን የኦሮሚያ ክልል መንግስት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ግድያው የተፈጸመው በመጋቢት ወር 2013ዓ.ም ነበር፡፡
ግድያው በምሽት መፈጸሙን እና 50 ሰዎችን በግድ ከቤታቸው በማውጣት በተፈጸመው ጥቃት 28 ሰዎች ሲገደሉ 12 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በንጹሃን ላይ የደረሰውን ጥቃት አውግዘው፤የአጸፋ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸው ነበር፡፡
በምስራቅ ወለጋ ዞን በተመሳሳይ ንጹሃን ተገድለዋል፡፡ ግድያው የተፈጸመው ነሐሴ 2013ዓ.ም ነበር፡፡ ኢሰመኮ በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪራሙ ወረዳ በተፈጸመው ጥቃት 150 ሰዎች መገደላቸውን መረዳቱን ገልጾ ነበር፡፡ ኢሰመኮ በወቅቱ ባወጣው መግለጫ ኦነግ ሸኔ ናቸው በተባሉ ታጣቂዎች በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የብሄር ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት ማድረሳቸውን መግለጹ ይታወሳል፡፡
ኢሰመኮ የኦሮሚያ ክልል እና የፌደራል የጸጥታ ኃይሎች ቅንጅት በመፍጠር የምስራቅ ወለጋ ነዋሪዎችን ደህንነት ማረጋገጥ አለባቸው ሲል አሳስቦ ነበር፡፡ በመስከረም ወር በኪራሙ ወረዳ ከ40ሺ በላይ ንጽሃን ሰዎች ጥቃት ሸሽተው መፈናቀናቸው እና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ የገለጸው ኢሰመኮ በወረዳው የሲቪል ሰዎች ደህንነት አደጋ ውስጥ መግባቱን ገልጿል፡፡
ጥቅምት ወር ላይ አል ዐይን አማርኛ ያነጋገራቸው የኪራሙ ወረዳ ነዋሪዎች “በአማራ ማንነታቸው ብቻ” ጥቃት እየደረሳባቸው እንደሆነ እና መንግስት እንዲደርስላቸው እንደሚፈልጉ ገልጸው ነበር፡፡
በንጽሃን ላይ የሚፈጸው ጥቃት ወደ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋና ወደ ቀሌም ወለጋም ተፈጽሟል፡፡ በመጋቢት ወር 2013ዓ.ም በሆሮ ጉዱሩ ዞን ነዋሪዎች በማንነታቸው ምክንያት ጫና እየደረሳባቸው መሆኑን በዞኑ ማንነትን መሰረት ያደረገ ግድያ እንዳል ተናግረዋል፡፡በዞኑ በአቤ ደንጎሮ ወረዳ ቱሉ ገና ቀበሌ በርካታ ሰዎች በማንነታቸው ተለይተው መገደላቸውም ተዘግቧል፡፡
በቅርቡ (በጥር ወር መጨረሻ አካባቢ) በቄለም ወለጋ ዞን በጊዳሚ ወረዳ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሸኔ በወረዳው የተለያዩ አካባቢዎች ዘግናኝ ግድያዎችን መፈጸሙን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የዞኑን ዋና አስተዳዳሪ ኢብሳ በሻን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ በጥቃቱ በአጠቃላይ 168 ሰዎች ሲገደሉ ከእነዚህ ውስጥ 87ቱ በጅምላ ተገድለው አስከሬናቸው አንድ ቦታ የተገኙ መሆናቸውን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል መንግስት በወለጋ ዞኖች ንጹሃን ሰዎች መገደላቸውን ቢገልጽም ግድያው ማንነት ላያ ያነጣጠረ አይደለም ይላል፡፡ የሚፈጸሙ ግድያዎችን ተከትሎ ክልሉ ጥቃት የሸኔ ታጣቂች መደምሰሱን ቢገልጽም ነዋሪዎች እስካሁን የመገደልና የመፈናቀል ስጋት ውስጥ መሆናቸውን እየተናገሩ ነው፡፡
የጥቃቱ ሰለባ ነዋሪዎቹ ስለ ጥቃቱ ምን ይላሉ?
አቶ እሸቱ ውበቱ የተወለደው በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ሲቡስሬ ወረዳ ሲሆን እስካሁንም በወረዳው ሲኖር ነበር፡፡
የ28 ዓመቱ አቶ እሸቱ ምንም እንኳን በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ተወልዶ ቢያድግም አሁን ግን ተወልዶ ያለበትን ቀየ ከለቀቀ 90 ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ ካለፈው ጥቅምት 20 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተፈናቃይ እንደሆነ የሚናገረው አቶ እሸቱ አሁን ምን ማድረግ እንዳለበት ለራሱም ጭምር ጥያቄ ውስጥ እንደሆነበት ለአል ዐይን አማርኛ ገልጿል፡፡
አቶ ውበቱ ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን በመሸሽ አሁን ላይ ደብረ ብርሃን የመጣበት ምክንያት በክልሉ ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት እየተባባሰ በመምጣቱ መሆኑን ለአል ዐይን አማርኛ ተናግሯል፡፡ አቶ ውበቱን ጨምሮ በርካታ ዜጎች በሚኖሩበት በሲቡስሬ ወረዳ ዜጎች ማንነታቸው አማራ በመሆኑ ብቻ የጥቃት ኢላማ ውስጥ እንደገቡ ተናግሯል፡፡
ሌላኛው ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀለው የ 38 ዓመቱ ፈረደ አለምነውም አሁን ላይ ተፈናቃይ ሆኖ በደብረ ብርሃን ከተማ ይገኛል፡፡
አል ዐይን አማርኛ አቶ ፈረደን ጨምሮ ለሌሎች ከኦሮሚያ ክልል ለተፈናቀሉ ዜጎች፤ በአካባባው ያለው ተደጋጋሚ ግድያ ለምን መቆም አልቻለም? የግድያው መነሻ ምክንያት ምንድነው? ዜጎችን የሚገድለውስ ማነው የሚለ ጥያቄዎችን አንስቷል፡፡
አስተያየታቸውን የሰጡት ተፈናቃዮች እንደሚሉት መንግስት ግድያውን የሚፈጽመው ኦነግ ሸኔ የሚባለው ቡድን እንደሆነ እንደሚገልጽላቸው ተናግረዋል፡፡ የክልሉ መንግስት ግድያውን ለማስቆምና እናንተን ለማትረፍ ምን ሰርቷል? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ተፈናቃዮቹ፤ ልዩ ኃይል እንደሚላክና የተላከው ልዩ ኃይል ወደመጣበት ሲመለስ ግድያው እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
መንግስት ግድያውን ለማስቆም ኃላፊነቱን ተወጥቷል?፤ ማስቆምስ ይችላል?
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ አሁን ላይ “ሸኔ” በዋነኝነት ጉዳት እየደረሰ ያለው አንድ የሆነ ማህበረሰብን ለይቶ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ “ሸኔ” በኦሮሚያ ክልል አመራር ሳይቀር ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
ዶ/ር ለገሰ ሁለቱን ብሔሮች ለማጋጨት በማለም አማራውን ነጥሎ የመምታት ሁኔታ እንዳለ የገለጹ ሲሆን ቡድኑ ይህንን የሚያደርገው እየተወሰደበት በመጣው እርምጃ ተስፋ በመቁረጥ እና ለማካካሻ እንደሆነ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በአብዛኛው የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የ“ሸኔ” ኃይል መደምሰሱንና መንግስትም አካባቢዎቹን እያጸዳ በቁጥጥር ስር እያደረገ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ምንም እንኳን ሚኒስትሩ “ሸኔ” በዋነኝነት ጉዳት እየደረሰ ያለው አንድ የሆነ ማህበረሰብን ለይቶ እንዳልሆነ ቢገልጹም አል ዐይን አማርኛ ያነጋገራቸው ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ የአማራ ብሔር ተወላጆች “አማራ በኦሮሚያ ውስጥ መኖር የለበትም” የሚል ንግግር በአካባቢው እንደተደመጠ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የቀድሞ የምስራቅ ወለጋ ዞን ሲቡስሬ ወረዳ ነዋሪዎች የአሁኖቹ ተፈናቃዮች አሁንም በስፍራው የታገቱና ህይወታቸው አደጋ ላይ የሆኑ በማንነታቸው አማራ የሆኑ ዜጎች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡
“ራቁታችሁን መጥታችሁ አሁን ከእኛ በላይ ሆናችሁ” የሚል ተደጋጋሚ ንግግርና ዛቻም እንደነበር ያነሱት ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች “የታገቱ ሰዎች ካልተፈቱ፤ ድርድር ተደርጎ ይህ ግድያ ካልቆመ” በኦሮሚያ ክልል መኖር ከባድ ነው ይላሉ፡፡
የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ (ዶ/ር) በ” ሕብረ ብሔራዊ ዘመቻ” ወቅት የመንግስት ዋነኛ ትኩረት በሰሜኑ ክፍል የነበረው ሁኔታ በመሆኑ፤ በኦሮሚያ ክልል “የወያኔ ተላላኪ በሆነው ሸኔ” ህብረተሰቡ ላይ ችግር እየደረሰ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
“ሸኔ”ን በሚፈለገው ፍጥነት ማስወገድ ያልተቻለው በመጀመሪያው ዘመቻ መንግስት ወደ ሰሜን አተኩሮ ስለነበር እንደነበር ዶ/ር ለገሰ ቢገልጹም በሰሜን ያለው ጦርነት ከመከሰቱ በፊትም ግድያዎች ሲፈጸሙ ነበር፡፡
ሚኒስትሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማለትም ከ15 ከ 20 ቀናት ወዲህ የመከላከያ ሰራዊት በዋነኝነት ትኩረት አድርጎ እየሰራ የሚገኘው በኦሮሚያ ውስጥ ያለውን የፀጥታ ሁኔታ ፈር የማስያዝ እንደሆነ ለአል ዐይን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም መሰረት በርካታ ቦታዎች ላይ ሸኔ እንደማሰልጠኛ ይጠቀምባቸው የነበሩትን፣ አንዳንድ ይዘዋቸው የነበሩ አካባቢዎች ላይ በወሰደው እርምጃ በ”ሸኔ” ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋና ምስራቅ ወለጋ በከፍተኛ ደረጃ “ሸኔ” በመከላከያ እና በክልሉ ልዩ ኃይል መመታቱንም አቶ ለገሰ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በአብዛኛው የኦሮሚያ አካባቢዎች የ”ሸኔ ኃይል” መደምሰሱን የገለጹት ዶ/ር ለገሰ ይህንን ተከትሎ መንግስትም አካባቢዎቹን እያጸዳ በቁጥጥር ስር እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
አልፎ አልፎ “ሸኔ” በሕብረተሰቡ ውስጥ በተለያየ መልክ የጸጥታ አካላት የሌሉባቸውን አካባቢዎች እንደዚህም ደግም የጸጥታ አካላት “አጽድተን አልፈናል” ያሏቸው አካባቢዎች ላይ ህብረተሰቡን መስለው እዛው ህብረተሰቡ ውስጥ በመደበቅ የሽፍታ መልክና ባህሪ ይዘው ህዝብ ላይ ጉዳት እያደረሱ ያሉ አሁንም አሉ ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡
ሰሞኑን በጎሃ ጺዮንም የተከሰተው ድርጊትም ከዚህ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ገልጸው አሁን ግን መንግስት በተጠናከረ መልክ እርምጃ እየወሰደ መሆኑንና በአጭር ጊዜ ውስጥም ይህ ችግር እንደሚፈታ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ ጉዳዩ የመንግስት ኃላፊነትን የመወጣት አለመወጣት አይደለም፤ በተለያየ መልክ የሚንቀሳቀሱ አካላት ባህሪ ነው፤ በእያንዳንዱ ቦታ ሰራዊት ልታሰፍር አትችልም፤ የህብረተሰብ ንቅናቄ ያስፈልጋል፤ ሕዝቡም እራሱን አደራጅቶ እራሱን መጠበቅ አለበት፡፡
ቀደም ብሎ መንግስት ትኩረቱን ወደ ሰሜን አድርጎ ነበር፤ በዚህ ወቅት በራሳቸው ማንሰራራት ነበር፤ ከዛ ውጭ በየጫካው 10ና 20 እየሆኑ ሰላማዊ ዜጋ መስለው ነው የሚጠቁት ይህንን የማጥራት ስራ ይጠይቃል፡፡ መንግስትም የቆየበት ተልዕኮ ስለነበር የተፈጠረ ነው እንጅ መንግስት ቸልተኛ ሆኖ አሊያም ከነአካቴው መስራት ካለመፈለግ የመጣ አይደለም፡፡
የኦሮሚያ ክልል ምን ይላል?
የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና ጸጥታ ም/ቢሮ ኃላፊ ኮሎኔል አበበ ገረሱ በክልሉ ያለውን የጸጥታ ችግር ክልሉ ለምን መፍታት ተሳነው የሚል ጥያቄ ከመንግስታዊው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርቦላቸው ነበር፡፡
ኮ/ል አበበ አመራሩ በሪፎርም ሂደት ውስጥ የመጣ እንጅ በስር ነቀል የመጣ አይደለም ብለዋል፡፡
እንኳን አዳዲስ ወጣቶች ቢጨመሩም ገዥው ፓርቲ ብልጽግና ውስጥ የነበሩት ከዚህ በፊት ኦዲፒ ከዛ በፊትም ኦህደዴ በሚለው ስያሜ ውስጥ የነበሩ ናቸው ብለዋል፡፡በዚህ ሂደት ውስጥ ፈተናዎች እንደነበሩ ያነሱት ኮ/ሉ የክልሉን መዋቅሩ የሚጠራው በሂደት እንጅ በአንድ ጊዜ አለመሆኑን አንስተዋል፡፡
የክልሉ አስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ የክልሉ መዋቅር ራሱን እየገመገመ እንደሆነ ያነሱት ኮ/ሉ ወላዋይ ኃይል በክልሉ ቦታ እንደሌለው አንስተዋል፡፡
?የዜጎች ደህንነት እንዴት ይረጋገጥ
በኦሮሚያ ክልል በየጊዜው ተመሳሳይ የማንነት ግድያዎች እየተከሰቱ ነው፣ ድርጊቱ የዜጎችን በህይወት የመኖር እና ሌሎች ሰዎች ሰው በመሆናቸው በተፈጥሯቸው ያገኟቸውን መሰረታዊ መብቶችን የሚጋፋ ነው ብለዋል፡፡
ግድያውን እነማን ናቸው እየፈጸሙ እና እያስፈጸሙ ያሉት፣ ተዋንያኖቹ እነማን ናቸው በሚል ተጠንቶ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት አቶ የህግ ባለሙያና የጥናት አማካሪ ቶማስ ተናግረዋል፡፡
የግድያው እና ማፈናቀሉ ተዋንያን መለየት አለባቸው፣ተገቢው ጥቃት በአጥፊዎች ላይ መጣል አለበት፣ በዚህ ድርጊት የተሳተፉ ሰዎች፣ ቡድኖች ወይም ተቋማት በመለየት ከህብረተሰቡ እንዲነጠሉ መሰራት አለበትም ብለዋል፡፡
ይህ ካልሆነ ግን ግድያዎቹ እና ማፈናቀለቹ መቀጠላቸው አይቀርም የሚሉት የሕግ ባለሙያው በተለይም ግድያ እና ማፈናቀሉ ይቀጥላል የሚለው አስተሳሰብ እየጨመረ ይሄዳል ሲሉም አክለዋል፡፡
ችግሮች እንደሚፈቱ እና አንድ ቀን አጥፊዎች ተለይተው ቅጣት የሚጣልበት አሰራር እንደሚዘረጋ ተስፋ አደርጋለሁ ሲሉም የሕግ ባለሙያው ነግረውናል፡፡
ኢሰመኮ የሰብአዊ ምን ይላል?
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ) ምክትል ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ለአል ዓይን እንደገለጹት ኦሮሚያን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች የሚፈጸሙ ማንነት ላይ መሰረት ያደረጉ ግድያዎች የፖለቲካ መፍትሄዎችን የሚፈልግቡት ደረጃ ላይ ደርሰዋል ብለዋል፡፡
ኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እያጣራ የምርመራ ሪፖርቶችን እና የመፍትሄ ሀሳቦችን ለሚመለከታቸው ተቋማት ሲያሳውቅ ቆይቷል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሯ በህግ የተሰጠው ስልጣንም ሰብዓዊ መብቶች ሲጣሱ ማሳሰብ እና ማሳወቅ ላይ የተመሰረተ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ ማንነትን መሰረት ያደረጉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ስላልቆሙ እና እየተበራከቱ ስለመጡ ጉዳዩ ፖለቲካዊ መፍትሄዎች በሚያስፈልጉበት ደረጃ ላይ መድረሱን አክለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በትናንትናው እለት በህዝብ ተወካዮች ምክረቤት ቀርበው ኦነግ ሸኔ “የፖለቲካ ግቡ ምን እንደ ሆነ የማይታወቅ እና ለሰው ልጆች ክብር የሌለው ቡድን ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“የጸጥታ አካላት በየስፍራው የተመደቡ ቢሆንም፣ ጥቃቱን የሚፈጽመው በቀጥታ ውጊያ ሳይሆን በመሽሎክሎክ ነው። የበረታው የሚያሰለጥኑት ኃይሎች ስለ በዙና ተገን የሚሆነው ስላገኘ ነው። የሚያስጠጋውን ህዝብ ቀርበን ቅራኔውን መፍታትና ነገሮችን ማስተካከል ይጠበቅብናል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡፡