የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል ተከበረ
የኃይማኖት አባቶች ግጭትና የእርስ በእርስ ጦርነት ሊቆም ይገባል ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል
ለሀገርና ህዝብ ሰላም የኃይማኖት አባቶች በጋራ እንዲሰሩም ጥሪ ቀርቧል
የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል (ፋሲካ) በመላው ኢትዮጵያ በተለያዩ ኃማኖታዊ እና ባህላዊ ስርዓቶች ተከበረ።
በተለይም የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያን በልዩ የማህሌትና የቅዳሴ ስነ-ስርዓት ተከብሯል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ለብርሃነ ትንሳኤው በሰላም አደረሳችሁ ሲሉ ቃለ በረከት አድርሰዋል።
"...እንዳለመታደል ሆኖ የሰው ልጆች ዛሬም ምርጫቸው ትንሣኤ ሳይሆን ሞት ሆኖ መገኘቱ እጅግ በጣም የሚቆጭና የሚያሳዝን ነው" ያሉት አቡነ ማትያስ፤ ንስሐ መግባት መፍትሄ ነው ብለዋል፡፡
"ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት፤ ይህ የኔ ነው ይህ የኔ ነው በሚል ደካማ አመለካከት ራሳችንን በራሳችን አንጉዳ፣ ከእንግዲህ ወዲህ የጥይት ድምፅ ይብቃ" ሲሉ የበዓሉን ዓቢይ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በዓሉን የተራቡትን በመመገብ፣ የታረዙትን በማልበስ፣ የተጨነቁትን በማጽናናት፣ እንዲሁም የተገኘውን የሰላም ጭላንጭል ይበልጥ ለማስፋትና የሀገር አንድነቱን በዕርቅ ዘላቂ ለማድረግ ቃል በመግባት እንዲከበርም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሀነ ኢየሱስ እንኳን ለትንሳኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ብለው፤ ትንሳኤ ልዩነትን ያሸነፈ በዓል መሆኑን ተናግረዋል።
"ግጭት፣ ሰቆቃ፣ ስደትና የእርስ በእርስ ጦርነት ሊቆም ይገባል" ብለዋል።
የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የኢትዮጵያን ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስትያናት ካውንስል ጠቅላይ ፀኃፊ ቄስ ደረጄ ጀምበሩ፤ የኃይማኖት አባቶች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተቀራርበው መስራት አለባቸው ብለዋል።
"ለሀገርና የህዝብ ሰላም ቅድሚያ በመስጠት በጋራ እንሰራ ዘንድ ካውንስሉ ወንድማዊ ጥሪውን ለመንፈሳዊ አባቶች በአክብሮት ያስተላልፋል" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።