ኢትዮጵያ ለጸጥታው ምክር ቤት ተሰጥቷል ባለችው “በእውነታ ላይ ያልተመሰረተ ገለጻ” መስጋቷን ገለጸች
የጸጥታው ምክር ቤት (UNSC) ትናንት የኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች ላይ በዝግ መምከሩ የሚታወስ ነው
“ገለጻው የመንግስትንና የሌሎች ሰብዓዊ አጋሮችን ጥረት ዝቅ ያደረገ እና የሚያደናቅፍ” መሆኑን አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ተናግረዋል
ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታዎች ማስተባባሪያ ተቋም (OCHA) ትናንት ለተሰበሰበው የድርጅቱ የጸጥታው ምክር ቤት (UNSC) ሰጥቷል ባለችው “በእውነታ ላይ ያልተመሰረተ ገለጻ” መስጋቷን ገለጸች፡፡
ገለጻውን በማስመልክት በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ከተቋሙ (OCHA) ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጋዳ ኤል ጣሂር ጋር መወያየታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ተቋሙ ለምክር ቤቱ “በሰጠው ጠቃሚ ያልሆነ ገለጻ መስጋታችንን ገልጸናል”ያሉት አምባሳደር ታዬ “ገለጻው የመንግስትንና የሌሎች ሰብዓዊ አጋሮችን ጥረት ዝቅ ያደረገ እና የሚያደናቅፍ” መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
“ችግሮችን ለመሻገር የሚያስችልና በእውነታ ላይ የተመሰረተ አካሄድ አስፈላጊነት ላይ” ከምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ጋር በአጽንኦት መወያየታቸውንም ነው አምባሳደር ታዬ በይፋዊ የማህበራዊ ገጻቸው ያሰፈሩት፡፡
ማርክ ሎውኩክ የተባሉት የOCHA ዋና ዳይሬክተር ትናንት ለምክር ቤቱ ገለጻ ባደረጉበት ወቅት በትግራይ ክልል ያለው ሰብዓዊ ሁኔታ “ይበልጥ እየተባባሰ” መምጣቱን እና ጾታዊ ጥቃቶች “አሁንም በጦርነቱ መሳሪያ ሆነው እያገለገሉ” እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
“በተገባው ቃል መሰረት የኤርትራ ወታደሮች ከክልሉ እየወጡ አይደለም” ሲሉ ማብራራታቸውንም ነው እንደነ ኤኤፍፒ ዓይነት ዓለም አቀፍ ብዙሃን መገናኛዎች የዋና ዳይሬክተሩን ንግግር ዋቢ አድርገው የዘገቡት፡፡
ይህን “ይበልጥ እየከፋና እየተባባሰ የመጣ የሰብዓዊ ቀውስ ሁኔታ ከተኩስ አቁም ውጭ ለማስቆም እንደማይቻል” ስለመናገራቸውም ተዘግቧል፡፡
“በግጭቱ የተፈናቀሉ 4 ሰዎች በርሃብ ሞተዋል” የሚል ሪፖርት በዚህ ሳምንት መቀበላቸውንም ሎውኩክ ገልጸዋል፡፡
በሌሎች አጀንዳዎችም ላይ በዝግ የመከረው የጸጥታው ምክር ቤት (UNSC) ስብሰባ በምክር ቤቱ የአሜሪካ ተወካይ በአምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ የተጠራ ነው፡፡
አምባሳደር ሊንዳ የስብሰባውን መጠናቀቅ አስመልክቶ ባወጡት መግለጫ “በክልሉ ካሉ ሰብዓዊ የመብት ጥሰቶች ጋር የተያያዙ ሪፖርቶች አሁንም እየደረሱኝ ይገኛሉ”ብለዋል፡፡
ከዚህም ቀደም ሲል በተመድ እና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በተደረሰው ስምምነት መሰረት በክልሉ “ተፈጸሙ” በተባሉት ሰብዓዊ የመብት ጥሰቶች ላይ “ገለልተኛ ምርመራዎች መደረጋቸው እንዲቀጥል” ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ “መንግስት በወንጀለኞች ላይ እርምጃ ይወስዳል” ማለታቸውን ያደነቁት አምባሳደሯ “የኤርትራ መንግስት መሰል እርምጃዎችን እንዲወስድ” ጠይቀዋል፡፡