ኢትዮጵያ “ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው”ያለችውን የአሜሪካ ህግ መወሰኛ ምክር ቤት የውሳኔ ሃሳብ ተቃወመች
ኤምባሲው በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ከፍተኛ ስጋት መሆኑንም ነው በመግለጫው ያስቀመጠው
የውሳኔ ሃሳቡ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው ሲል ዋሽንግተን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ መግለጫ አውጥቷል
የአሜሪካ ህግ መወሰኛ ምክር ቤት ከቀናት በፊት በፈረንጆቹ ግንቦት 19 ቀን 2021 በኢትዮጵያ የተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ሊሻሻሉ ይገባል ባላቸው አጀንዳዎች ዙሪያ የውሳኔ ሀሳብ አሳልፏል።
ሴኔቱ የውሳኔ ሀሳብ ካሳለፈባቸው ጉዳዮች መካከል መንግስት ከህወሓት ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ይፈጽም፣ በትግራይ ክልል የሰብአዊ መብት ጥሰትን ማስቆም፣ ሁሉን አቀፍ አገራዊ የፖለቲካ ምክክር ይደረግ፣ የታሰሩ ጋዜጠኞች እና የፖለቲካ አስረኞች ይፈቱ ዋናዎቹ ናቸው።
ኢትዮጵያም በውሳኔ ሀሳቡ ላይ መበሳጨቷን ገልጻ ይህ የውሳኔ ሰነድ የሁለቱን አገራት ታሪካዊ ወዳጅነት የሚጎዳ ነው ስትል በዋሽንግተን ባለው ኤምባሲዋ በኩል ገልጻለች።
የኤምባሲው ምላሽ ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ከ120 ዓመት በላይ ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ያላቸው አገራት ናቸው ይላል።
ሁለቱ አገራት ያላቸው ግንኙነት ለአፍሪካዊያን ምሳሌ የሚሆን ነው ያለው ኤምባሲው ይህ የውሳኔ ሀሳብ አገራቱ በምስራቅ አፍሪካ እያደረጉት ያለውን ሽብርተኝነት የመዋጋት ስራ ይጎዳል ብሏል።
ኢትዮጵያ ለትግራይ ክልል በራሷ እና በረድኤት ተቋማት በኩል ለተፈናቃዮች ድጋፍ እያደረገች መሆኗን ገልጻ እስካሁን አሜሪካንን ጨምሮ ሌሎች አገራት ያደረጉት ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን ቀደም ሲልም አስታውቃለች።
ይሁንና ህግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ከህወሓት ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ይደረግ ሲል ያሳለፈው የውሳኔ ሀሳብ በፌደራል መንግስት እና ህወሓት መካከል ያለውን አለመመጣጠን ካለመረዳት የመነጨ ነው ብሎታል ኤምባሲው በመግለጫው በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት በዓለም አቀፍ የሽብርተኞች የመረጃ ቋት መካተቱን በመጠቆም፡፡
ሰሜን እዝን በማጥቃት ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ድቀት ያስከተለው ህወሓት አሜሪካ እና ኢትዮጵያ በጋራ ሲዋጉለት ለቆዩት ምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ከፍተኛ ስጋት እንደሆነም ነው ኤምባሲው ያስታወቀው፡፡
ምክር ቤቱ በትግራይ ያለውን የሰብአዊ እርዳታዎች ሂደት በተመለከተ ያሳለፈው የውሳኔ ሀሳብ ከእውነታው የተቃረነ እንደሆነም ገልጿል፤ የረድዔት ድርጅቶች ነጻ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ መፈቀዱንና መንግስት 70 በመቶ ያህል እርዳተዎችን መሸፈኑን በማከል፡፡
በክልሉ ያጋጠመው የመሰረተ ልማት ውድመት በህወሓት የተፈጸመ መሆኑንም ምክር ቤቱ ዘንግቶታልም ብሏል ኤምባሲው፡፡
ሆኖም መንግስት ባደረገው ከፍተኛ ጥረት የወደሙት መሰረተ ልማቶች ተጠግነው የስልክ እና ሌሎችም አገልግሎቶች መጀመራቸውንም ነው የገለጸው፡፡
በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት የታሰሩ የተቃዋሚ መሪዎች፣ ደጋፊዎቻቸው፣ አክቲቪስቶች እና ጋዜጠኞች ይፈቱ ለሚለው የምክር ቤቱ የውሳኔ ሃሳብም እንዲህ ያሉ እስረኞች በኢትዮጵያ የሉም ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡
በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት በአስር ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች የታሰሩት በህወሓት የአገዛዝ ዘመን እንደነበር በማስታወስም እስረኞቹ በለውጡ አመራር ተለቀዋል ብሏል፡፡
የውሳኔ ሃሳቡ በኢትዮጵያ የፍትህ ተቋማት በተያዙ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ የሚገባ እንደሆነም አስቀምጧል፡፡
ሃገር አቀፍ የውይይት እና የእርቅ መድረኮች እንዲፈጠሩ ያቀረበው ጥሪ መንግስት ከአሁን ቀደም 41 አባላት ያሉት የእርቀ ሰላም ኮሚሽንን በአዋጅ በማቋቋም በማድረግ ላይ ካላቸው ጥረቶች ጋር የሚሄድ ነውም ብሏል፡፡
አሉ የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በመንግስታቱ ድርጅት ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና በኢትዮጵያ ሰብአዊ መበት ኮሚሽን አማካኝነት እንደሚመረመሩም ገልጿል። የድርጊቱ ፈጻሚዎች ተለይተው ክስ መመስረቱንም አስታውቋል።
በአጠቃላይ ትግራይ ክልል ወደ ቀድሞ ሰላሟ እንደትመለስ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መገንባት፤ተፈናቃዮችን ከመደገፍ ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ ስራዎችን በመከናወን ላይ ናቸው ብሏል።
ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፎችን ለማድረግ እና ክልሉን ወደ ቀደመ እንቅስቀሴው ለመመለስ ዩኤስ ኤይድን ከመሳሰሉ ዓለም አቀፍ የረድኤት ተቋማት ጋር መስራቷን እንደምትቀጥልም ነው ኤምባሲው ያስታወቀው፡፡