ኢትዮጵያ በየቀኑ ከ70 ሺህ በላይ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ እያጓጓዘች መሆኑን አስታወቀች
እስከ ዛሬ ድረስ 2 ነጥብ 8 ሚሊየን የአፈር ማዳበሪያ ሀገር ውስጥ መግባቱን የግብርና ኮርፖሬሽን አስታውቋል
የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በማዳበሪያ ዋጋና አቅርቦት ላይ የፈጠረው ጫናስ ምን ይመስላል…?
በየቀኑ ከ70 ሺህ በላይ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ኮርፖሬሽን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ኮርፖሬሽን ለአል ዐይን አማርኛ እንዳለው በኢትዮጵያ የአፈር ማዳበሪያ በፍላጎቱ ልክ በአገር ውስጥ አለ ብሏል።
ከሰሞኑ በሀገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች የአፈር ማዳበሪያ እጥረት እንዳለ እና የዋጋ ጭማሪ ችግሮች መከሰታቸው ሲነገር ሰንብቷል።
የኮርፖሬሽኑ ኮሙንኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጋሻው አይችሉህም ለአል ዐይን እንዳሉት በ2014/15 ዓ.ም ለግብርና ስራዎች 12 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ያስፈልጋታል።
ዓመታዊ የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎቱ በግብርና ሚንስቴር የተጠና መሆኑን የሚናገሩት አቶ ጋሻው፤ ካለፈው ጥር 2014 ዕ.ም ጀምሮ ከ3 ሚሊየን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ ላይ መድረሱንና ከዚህ ውስጥ 2.8 ሚሊየን ኩንታሉ ወደ ሀገር ውስጥ መጓጓዙን አክለዋል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ከሞሮኮ እና አረብ ኢምሬትስ ዩሪያ 5 ሚሊየን ኩንታል እንዲሁም NPS 2 ነጥብ 18 ሚሊየን ኩንታል እንዲሁም NPSB የተሰኘው የአፈር ማዳበሪያ 5 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ የግዥ ውል መፈጸሟንም አቶ ጋሻው ገልጸዋል።
እስከ መጋቢት 20 ቀን 2014 ዓ.ምድረስም 3 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ የደረሰ ሲሆን፤ የአፈር ማዳበሪያ መጠን ከዚህ ውስጥ 2.8 ሚሊየን ኩንታል ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጉዟል ብለዋል።
860 ሺህ 140 ኩንታል ማዳበሪያ ደግሞ በጅቡቲ ወደብ ላይ ላይ ነው ያሉት አቶ ጋሻው በየዕለቱም ከ70 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ በመጓጓዝ ላይ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም መጋቢት 29 ቀን 2014 ዓ.ም 580 ሺህ 120 ኩንታል ማዳበሪያ የጫነች መርከብ ጅቡቲ ወደብ እንደምትደርስም ይጠበቃል ተብሏል።
600 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ የጫነች ተመሳሳይ መርከብም እስከ ሚያዝያ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ጅቡቲ ወደብ ትደርሳለች ተብሎ እንደሚጠበቅም አቶ ጋሻው ነግረውናል።
የአፈር ማዳበሪያውን ከጅቡቲ ወደብ ወደ ክልሎች በማጓጓዝ ለዩኒየኖች የሚያስረክበው የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት (ኢባትሎአድ) ሲሆን፤ በመጨረሻም በክልል ዩኒየኖች አማካኝነት ማዳበሪያው ለአርሶ አደሮች በመሰራጨት ላይ መሆኑንም አክለዋል።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በኢትዮጵያ የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት ግዢ ላይ ተጽዕኖ አላሳደረም? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም "ኢትዮጵያ የማዳበሪያ ግዥ ስምምነቱን ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ስለተዋዋለች ለጊዜው ጦርነቱ በግዢው ላይ ያሳረፈው ተጽዕኖ የለም" ብለዋል።
ይሁንና ሩሲያ እና ዩክሬን ለአፈር ማዳበሪያ እምራች እና ለሌሎች ፋብሪካዎች ጥሬ እቃዎችን የሚያቀርቡ ሀገራት በመሆናቸው በቀጣይ የራሱ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል ብለዋል አቶ ጋሻው።
ኢትዮጵያ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ከሰሜን አፍሪካዋ ሞሮኮ እና አረብ ኢምሬትስ በፈረንጆቹ 2021 ላይ ስምምነት መፈጸሟን ከኮርፖሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።