አረብ ኢምሬትስ በመሬት መንሸራተት ጉዳት ለደረሰባቸውን ኢትዮጵያውያን የሰብዓዊ ድጋፍ ላከች
አረብ ኢምሬትስ 75 ቶን ምግብ ነክና ሌሎች ቁሳቁሶችን ድጋፎችን ነው የላከችው
በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ የደረሰበት ስፍራ አስከሬን የማፈላለጉ ስራ እንደቀጠለ ነው
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ አረብ ኢምሬትስ በዛሬው እለት በኢትዮጵያ በመሬት መንሸራተት ለተጎዱ ሰዎች ድጋፍ መላኳን አስታውቀዋል።
ሰብዓዊ ድጋፉ በፕሬዚዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ነህያን መመሪያ መሰረት በከባድ ዝናብ ምክንያት በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ኢትዮጵያውያን ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ መለኩን አል አይን ኒውስ ከዋም ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
የአረብ ኤሚሬትስ የእርዳታ ዓላማ በዚህ የተፈጥሮ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች አስቸኳይ ድጋፍ ለመስጠት መሆኑም ተመላክቷል።
የአረብ ኤሚሬትስ የዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ደኤታ ሪም ቢንት ኢብራሂም አል ሃሽሜይ፤ አረብ ኢምሬትስ ወዳጅ ሀገራት በችግር ጊዜ መደገፏን እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
ከአረብ ኢምሬትስ የተላከውን የሰብዓዊ ድጋፍ አስመልክቶ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ አረብ ኢምሬትስ 75 ቶን ምግብ ነክና ሌሎች ቁሳቁሶችን ድጋፎችን መላኳን እና ድጋፉ ዛሬ ጠዋት አዲስ አበባ ቦሌ ኤርፖርት መድረሱንም አስታውቀዋል።
የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከአረብ ኢምሬትስ የተላከውን ሰብዓዊ ድጋፍ ተቀብሎ በቀጥታ ለተጎጂዎች የሚያቀ,ደርስ መሆኑንም ሚኒስትር ደኤታዋ በመግለጫቸው አስታውቀዋል
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ አክለውም፤ የተባበሩት መንግስታትና የተለያዩ ሀገራት መሪዎች በሀገሪቱ ለደረሰው የመሬት መንሸራትት አደጋ የተሰማቸውን ሃዘን መግለጻቸውን ጠቁመዋል።
በተያያዘ ሚኒስትር ደኤታዋ፤ አደገጋው በድረሰበት ስፍራ ላይ እስካሁን የተገኘ አስከሬን ቁጥር 231 መድረሱን በመግለጽ፤ ተጎጂዎችን የመፈለጉ ስራ አሁንም መቀጠሉን አስታውቀዋል።
በአደጋው ከ500 በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን በመግለጽ፤ ለእነዚህ ዜጎች የአስቸኳይ ጊዝ እርዳታ በፌደራል መንግስት እና በተለያዩ አካላት የቀረበ በመሆንም አስረድተዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እርዳታ ማስተባበርያ ቢሮ (ኦቻ ) ባሳለፍነው ኃሙስ ባወጣው መግለጫው፤ መመሬት መንሸራተት አደጋው አደጋ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 257 መድረሱን መግለጹ ይታወሳል።
በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር እስከ 500 ሊደርስ እንደሚችል ያስታወቀው ኦቻ በአካባቢው የሚገኙ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ 15ሺህ ሰዎችን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማዘዋወር እንቅስቀሴ መጀመሩን ነው ይፋ ያደረገው።
አል ዐይን አማረኛ የፍለጋ ስራውን በተመለከተ ከጎፋ ዞን የኮምኒኬሽን ሃላፊ አቶ ካሳሁን ጋር ባደረገው ቆይታ አሁንም በእጅ ቁፋሮ ሰዎችን የማፈላለግ ስራው መቀጠሉን ሰምቷል።
ቁፋሮውን በኤክስ እስካቫተር እና በሌሎችም ማሽኖች ለማድረግ ሀሳቦች ቢኖሩም የአካባቢው መልክዓ ምድር አመች ባለመሆኑ ቁፋሮውን በሰዎች ሀይል ለመቀጠል ተወስኗል ነው ያሉት።