የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በአማራ ክልል ዙሪያ ያወጣው ሪፖርት ከእውነታ ያፈነገጠ ነው- መንግስት
ኢሰመኮ በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች የሚፈጸሙ ግድያዎች መቀጠላቸውን መግለጹ ይታወሳል
የአማራ ክልል ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እየተመለሰ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ሰሞኑን በአማራ ክልል መንግሥት ሰብአዊ መብቶችን እንደጣሰ በማመላከት ያወጣው ሪፖርት ከእውነታው ያፈነገጠ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አግልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ዛሬ ወቅታዊ ሁኔታን አስመለክተው በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥተዋል።
ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በመግለጫቸው፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ሰሞኑን በአማራ ክልል ውስጥ መንግሥት ሰብአዊ መብቶችን እየጣሰ መሆኑን የሚያመለክት ሪፖርት ማውጣቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርቱ፤ በአማራ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች በከባድ መሣሪያ እና አልፎ አልፎ በአየር/ድሮን ድብደባ ጭምር የታገዘ ነው ያለ ሲሆን በሲቪል ሰዎች ላይ ሞት እና የአካል ጉዳት መድረሱን አመላክቷል።
በሰሜን ሸዋ ዞን፣ በረኸት ወረዳ፣ መጥተህ ብላ ከተማ፣ በደብረ ማርቆስ ከተማ እንዲሁም በደንበጫ ከተማ በተፈጸመ የድሮን እና ከባድ መሳሪያ ጥቃት ሁለት ዓመት ያልሞላው ህጻንን ጨምሮ በርካታ ንጹሃን መገደላቸውን ነው ሪፖርቱ የጠቆመው።
በህክምና ላይ የነበሩ ሰዎችን ጨምሮ ቤት ለቤት በተደረገ ፍተሻ ሳይቀር ግድያ ተፈጽሟል ያለው ኢሰመኮ፤ በ200 ሴቶች ላይ የአስገድዶ መደፈር ወንጀል መፈጸሙንም በሪፖርቱ አሳውቆ ነበር።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አግልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በዚህ ዙሪያ በሰጡት ምለሽ፤ የኢሰመኮ ሪፖርት የመንግሥትን እንቅስቃሴ ዐውድ ከግምት ያላስገባ፣ በበቂ መረጃ ላይ ያልተመሠረተ እና ከእውነታ ያፈነገጠ መሆኑን ጠቁመዋል።
መንግሥት ገለልተኛ ተቋማት እንዲኖሩ የሚፈልገው የተዛቡ መረጃዎች አንዲታረሙ እና ዴሞክራሲ እንዲጠናከር አስቦ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ለገሰ፣ ነገር ግን እነዚህ ገለልተኛ ተቋማት በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ ባሉ የተዛቡ መረጃዎች ከተጠለፉ የምንፈልገውን ዴሞክራሲ ልንገነባ አንችልም ብለዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንም የሚያወጣቸውን መረጃዎች ከትክክለኛ መንጭ በመረዳት እና ትክክለኛውን ዐውድ ከግምት ያስገባ መሆን እንሚገባው፣ ለዚህም የሰሞኑን መግለጫውን ቆም ብሎ እንዲገመግም አሳስበዋል።
መንግሥት በአማራ ክልል ያለውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት እና የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት ለማረጋገጥ ጥንቃቄ የተሞላባቸው እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑንም ዶ/ር ለገሰ አረጋግጠዋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)መግለጫው አክለውም የአማራ ክልል ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እየተመለሰ መሆኑን እና በክልሉ በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መታደግ እንደተቻለ ገልጸዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ መምሪያው ተቀናጅቶ በመሰዳቸው ርምጃዎች ክልሉን ከመፍረስ መታደግም አልፎ በአዳዲስ አደረጃጀትና በአዳዲስ አመራሮች በማደራጀት ወደሰላም እንዲመለስ ማችቻሉን ገልጸዋል።
ዶ/ር ለገሰ፤ “ራሱን ፋኖ ብሎ የሚጠራው ጽንፈኛ ቡድን ወደ ተራ ሽፍትነት እንዲወርድ ተደርጎ፤ የክልሉ ፀጥታ ኃይል እግሩን መትከል መቻሉን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ግብረ-ኃይሉ አረጋግጧል” ብለዋል።
"አሁን ያሉት ቀሪ ሥራዎች የተንጠባጠበውን ጽንፈኛ ኃይል መልቀም እና በክልሉ ያለው አዝመራ ያለብክነት እንዲሰበሰብ ማድረግ ነው" ብለዋል ዶክተር ለገሠ ቱሉ፡፡
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ቁጥጥር ስር ከዋሉ 3 ሺህ 200 ዜጎች መካከል 1 ሺህ 51ዱ ወደቤተሰባቸው መቀላቀላቸውንም አስታውቀዋል።