በመንግስትና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ሸኔ) መካከል እየተደረገ ነው ስለ ተባለው ንግግር ምን አዲስ ነገር አለ?
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ሰላማዊ መፍትሄ ለመፈለግ ቁርጠኛ መሆኑን አስታወቀ
የኢትዮጵያ መንግስት በታንዛኒያ እየተካሄደ ነው ስለተባለው ድርድር እስካሁን አስተያየት አልሰጠም
በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥትና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ሸኔ) መካከል ሁለተኛ ዙር ንግግር በታንዛኒያዋ ዳሬሰላም እየተካሄደ መሆነ ታውቋል።
መንግሥት "ሸኔ" ብሎ በአሸባሪነት የፈረጀውና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ኃይል ትናንተ ባወጣው መግለጫ፤ ከፍተኛ አመራሮቹ በታንዛኒያ ከፌደራል መንግስት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን አስታውቋል።
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በመግለጫው በቡድኑ መሪ ጃል መሮ (ድሪባ ኩምሳ) እና በምክትላቸው ጃል ገመቹ አቦየ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ልዑካን ቡድን ዳሬሰላም እንደሚገኝም አስታውቋል።
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት የጦር አዛዦች በኦሮምያ ክልል ከሚገኙ ግንባሮች ካላቸው ቦታዎች ወደ ታንዛንያ የሚያደርጉት ጉዞ ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ዘግየት ብሎ መግለጹንም በመግለጫው አብራርቷል።
በኦሮሚያ ክልል ለአስርት ዓመታት የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ለሁለተኛ ዙር ለመነጋገር በታንዛኒያ መገኘቱን ያስታወቀው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት፤ ሰላማዊ መፍትሄ ለመፈለግ ቁርጠኛ መሆኑንም በመግለጫው አስታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በታንዛኒያ እየተካሄደ ነው ስለተባለው ድርድር እስካሁን አስተያየት አልሰጠም።
በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና መንግሥት "ሸኔ" ብሎ በአሸባሪነት የፈረጀውና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን መካከል ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ ድርድር እየተካሄደ ስለመሆኑ ተነግሯል።
ለአደራዳሪዎቹ ቅርበት ያላቸው እና ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ባለስልጣን ለሮይተርስ እንደተናገሩት፤ ውይይቱ ባለፈው ሳምንት በታንዛኒያ የንግድ መዲና ዳሬሰላም መጀመሩን እና ድርድሩ በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) እየተመቻቸ ነው።
በታንዛኒያ በቀጠለው ድርድር መንግሥትን ወክለው በድርድሩ ላይ እየተሳተፉ ከሚገኙት ወታደራዊ አመራሮች፣ በተጨማሪ የፖለቲካ አመራሮች ወደ እፍራው ማቅናታቸው ተነግሯል።
ቢቢሲ ምንጮች አረጋግጠውልኛል ብሎ ባወጣው መረጃ በመጀመሪያው ዙር ውይይት የኢትዮጵያ መንግሥት ተወካይ የነበሩት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዴዎን ጢሞቴዎስ ከቅርብ ቀናት በፊት ታንዛንያ መግባታቸውን አስነብቧል።
በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና በኦነግ ሸኔ መካከል ከወራት በፊት በታንዛኒያ ከፊል ራስ ገዟ ዛንዚባር ለድርድር ተተቀምጠው ንደነበረ እና ድርድሩ ያለ ስምምነት መጠናቀቁ ይታወሳል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2013 ግንቦት ወር ላይ በኦሮሚያ ክልል ታጥቆ የሚንቀሳቀሰውን "ኦነግ ሸኔ" ቡድን በሽብርተኝትነት መፈረጁ የሚታወስ ነው።