መንግስት ህወሓትን እና ሸኔን በሽብርተኝነት ልፈርጅ ነው ስለማለቱ ምሁራን ምን አሉ?
“ውሳኔው እንዲያውም ቢዘገይ እንጂ ትክክለኛ ውሳኔ ነው”- ሲሳይ መንግስቴ (ዶ/ር)
“ስጋት ሊሆን በማይችልበት ደረጃ ‘አጥፍተነዋል’ ያሉትን አካል ‘በሽብርተኝነት ልንፈርጅ ነው’ ማለት ምን ማለት ነው?”- ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ምሁር
መንግስት ህወሓትን እና ሸኔን በሽብርተኝነት ለመፈረጅ የሚያስችል የውሳኔ ሃሳብ ባሳለፍነው ቅዳሜ አቅርቧል፡፡
የውሳኔ ሃሳቡ ህወሓት እና ሸኔ “የሀገረ መንግሥቱን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል ተንቀሳቅሰዋል” በሚል ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበ ነው፡፡
በድርጅቶቹ ምክንያት “የበርካታ ዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፣ አካል ጎድሏል፣ንብረትው ወድሟል፣ በርካቶችም ከቀያቸው ተፈናቅለዋል” በሚል በሃሳቡ የተወያየው ምክር ቤቱ “ኅብረተሰቡ ቀጣይነት ባለው ሥጋትና ፍርሐት ውስጥ እንዲኖር፣ በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጣ፣ ዜጎች እርስ በእርስ እንዳይተማመኑ አድርገዋል” ሲል የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ መደገፉ የሚታወስ ነው።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ግን የውሳኔ ሃሳቡን ተቃውሟል፡፡ “የተጀመሩ ሰላማዊ የሽግግር ሂደቶችን ለማስተጓጎል ሆን ተብሎ የተደረገ ነው”ም ነው ዛሬ ባወጣው መግለጫ ያለው፡፡
አል ዐይን አማርኛም የውሳኔ ሃሳቡን በማስመልከት ተገቢነቱን፣ አንድምታውን እና ምን ያህል ችግሮች ሊፈታ እንደሚችል ምሁራንን አናግሯል፡፡
“በሽብርተኝነት ሊፈረጅ የሚችል አካል ለቁጥጥር ያስቸገረ ጠንካራ መዋቅር ያለው ነው” በሚል የሚናገሩ አንድ ስማቸውን ለመግለጽ ያልፈለጉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁር ጠቅላይ ሚኒስትሩ መከላከያው ጭምር ህወሓት ስጋት ሊሆን በማይችልበት ደረጃ “መመታቱን እና መዳከሙን ደጋግመው በአደባባይ በተናገሩ” ማግስት እንዲህ መባሉ ምን ለማለት ተፈልጎ ነው ሲሉ የውሳኔ ሃሳቡን ያጠይቃሉ፡፡
‘አጥፍተነዋል’ በሚል ሲነገር የነበረው “ፕሮፓጋንዳ እንደነበርና ህወሓት አሁንም ስጋት እንደሆነ የሚያሳይ ነው” ሲሉም ያስቀምጣሉ የመንግስትን ተዓማኒነት “ይበልጥኑ የሚጎዳ” መሆኑን በመጠቆም፡፡
በትግራይ ከተካሄደው “ህግ የማስከበር ዘመቻ” ጋር በተያያዘ አስከፊ ሰብዓዊ ጥሰቶች መፈጸማቸውን በመግለጽ ችግሩ “በሰላማዊ መንገድ በድርድር” እንዲፈታ ከተለያዩ የውጭ አካላት ጥያቄዎች እየቀረቡ ይገኛሉ፡፡
‘ሁኔታው አሳስቦናል’ በሚሉ የውጭ አካላት የሚቀርቡት እነዚህ ጥያቄዎች አሁን አሁን የጫና መልክም እየያዙ ነው፡፡
በሽብርተኝነት የመፈረጁ የውሳኔ ሃሳብ በዚሁ ሰበብ የመጣም ነው ይላሉ ቀደም ሲል የተጠቀሱት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው ምሁር፡፡
“በአሸባሪነት ከተፈረጀ አካል ጋር አንደራደርም በሚል ተጽዕኖውን ለመቋቋም በማሰብ የተደረገ” ሊሆን እንደሚችልም ያስቀምጣሉ፡፡
ሆኖም ከድርጅቶቹ ጋር “ግንኙነት አላቸው በሚል የሚጠረጠሩ አካላት ለተለያዩ በደሎች እንዳይዳረጉ፤ ለጭቆና በር እንዳይከፍት ስጋት አለኝ”ም ነው የሚሉት፡፡
መንግስት “ሸኔ” ሲል ስለጠቀሰው “ምንነቱና ማንነቱ የማይታወቅ አካል ሊጠየቅና ሊያብራራ” እንደሚገባም ይናገራሉ፡፡
“ታጥቆ ዜጎችን የሚገድለው ኦነግ ሸኔ ‘የመንግስት ድጋፍ አለው፤ የኦነግ እና የመንግስት ጥምር ጦር ነው’ እየተባለ ባለበት ሁኔታ ነጥሎ ‘ሸኔ’ ማለቱ ምን ማለት ነው?” ሲሉ የሚያጠይቁት ምሁሩ ሁኔታው “በመንግስት ይደገፋል መባሉን የሚያጠናክር እና ከለላ ለመስጠት በማሰብ የተደረገ” ሊሆን እንደሚችልም ይገልጻሉ፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ እና ፌደራሊዝም መምህሩ ሲሳይ መንግስቴ (ዶ/ር) ግን “ውሳኔ እንዲያውም ቢዘገይ እንጂ የሚጎዳ አይደለም” ሲሉ በጥሩ ጎኑ ያነሳሉ፡፡
እንደ ዶ/ር ሲሳይ ገለጻ “ህወሓትን ሽብርተኛ ብሎ ለመፈረጅ በሰሜን እዝ ላይ ያደረሰው ጉዳት ብቻ በቂ ነው”።
“ህወሓት ባለፉት 3 ዓመታት በግልጽ እና በስውር በርካታ ጥፋቶችን አድርሷል” የሚሉት መምህሩ “የዘገየ ግን ትክክለኛ” የውሳኔ ሀሳብ ቀርቧልም ብለዋል።
መንግስት በውሳኔ ሃሳቡ ኦነግ ሸኔ ከማለት ይልቅ ‘ሸኔ’ ማለቱ ምናልባትም “ለሌላ ትርጉም እንዳይጋለጥ በማሰብ ሊሆን ይችላል እንጂ ‘ሸኔ’ በሚል በኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናትን እና ሌሎች በክልሉ የሚኖሩ ማንኛውንም ማህበረሰብ እንደፈለገ እየገደለ ነው ይሄንን የሚያደርገው ደግሞ ኦነግ ሸኔ ነው” ብለዋል ዶ/ር ሲሳይ፡፡
“ሸኔ” እና “ኦነግ” አንድ ለመሆናቸው የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ባንድ ወቅት ለመገናኛ ብዙሃን በትጥቅ መፍታት ጉዳይ ሲጠየቁ “ማን ነው ትጥቅ ፈቺ፤ ማንስ ነው ትጥቅ አስፈቺ” በሚል የሰጡት መግለጫ በቂ ማስረጃ ነው ብለዋል።
ዶ/ር ሲሳይ መንግስት ትጥቅ እንዲፈቱ ሲጠይቅ ‘ወታደሮቻችን ትጥቅ የሚፈቱት ለመንግስት ሳይሆን ለአባገዳዎች ነው’ በሚል መንቀሳቀሳቸውንም በማስረጃነት ያነሳሉ፡፡
ጉዳዩን በዝርዝር የሚያየው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ‘ሸኔ’ በሚል የቀረበለትን ‘ኦነግ ሸኔ’ ብሎ ያስተካክላል የሚል ግምት እንዳላቸውም ተናግረዋል።
“ኦነግ ሸኔ በይፋ ሰዎችን የሚገድል የተደራጀ እና የታጠቀ ሀይል ነው፤ በአሸባሪነት መፈረጁ ዘግይቷል እንጂ ትክክል ነው” ሲሉም አስቀምጠዋል።
የሽብርተኝነት ውሳኔው በተለይም ኢትዮጵያ በህወሓት ጉዳይ ከአሜሪካ እና አውሮፓ ህብረት ለሚቀርብባት የተደራደሩ ጥያቄዎች መፍትሄ ሊሆን ይችላልም ብለዋል የውጭ ሃገራቱ በሽብርተኛ ቡድኖች ላይ ያላቸው አቋም እንደሚታወቅ እና ደፍረው የተደራደሩ ጥያቄዎችን ለኢትዮጵያ ላያነሱ እንደሚችሉ በመጠቆም፡፡
ከዚህ ባለፈም ህወሓት እና ሸኔ በአሸባሪነት ከተፈረጁ ያላቸው ገንዘብ፣ንብረት እና ሌሎችም ሀብቶች በሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር ስለሚውሉ ለኢትዮጵያ አንደ አገር ጥቅሙ ብዙ ይሆናልም ብለዋል።
ድርጅቶቹን በሽብርተኝነት የመፈረጁ የውሳኔ ሃሳብ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመርቷል፡፡
ምክር ቤቱም የውሳኔ ሃሳቡን አስመልክቶ ህወሓት እና ሸኔ ተቃውሞ ካላቸው ቅሬታ እንዲያቀርቡ ዛሬ ጠይቋል፡፡