መንግስት “በትግራይ ከ77ቱ ጋር የሚስተካከል ድርቅና ረሃብ ቀውስ ሊፈጥር ነው በሚል የተሰጠው መግለጫ ስህተት ነው” አለ
ትግራይ ከ1977ቱ ወደ ከፋ ረሀብ ልትገባ ጫፍ ላይ መድረሷን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደሩ አስታውቋል
መንግስት “በ100 ሺህ የሚቆጠር ታጣቂ ሰብስቦ የሚቀልብ አካል ስለ ትግራይ ህዝብ ስቃይ የማውራት ሞራል የለውም” ብሏል
በትግራይ ክልል ከ1977ቱ ጋር የሚስተካከል ድርቅና ረሃብ ቀውስ ሊፈጥር ወደሚችልበት ደረጃ እየተሸጋገረ ነው በሚል የተሰጠው መግለጫ ፈጽሞ ስህተት ነው ሲል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በዛሬው እለት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ፤ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተከሰቱ የድርቅ አደጋዎች ዙሪያ ማብራያ ሰጥተዋል።
በዚህም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ የድርቅ አደጋዎች ወደ ረሃብ ተቀይሯል መባሉን ስህተት ነው ብለዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫው “ትግራይ በመላው ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጉዳት ካስከተለው በደርግ ዘመነ መንግስት ከተከሰተው የ1977ቱ ርሃብ ወደ ከፋ የረሀብ አደጋ ውስጥ ልትገባ ጫፍ ላይ ደርሳለች” ብሏል።
በትግራይ የነበረው አውዳሚ የጦርነት አሻራ እና ድርቅ ያስከተለው ረሀብ አደጋኛ ጥምረት መፍጠራቸውን የገለጸው ጊዜያዊ አስተዳደሩ "90 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ለረሀብ እና ለሞት ተጋለጭ ሆኗል" ብሏል።
የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)፤ “ከሰሞኑ በትግራይ ክልል ከ77ቱ ጋር የሚስተካከል ድርቅና ረሃብ ቀውስ ሊፈጥር ወደሚችልበት ደረጃ እየተሸጋገረ ነው በሚል የተሰጠው መግለጫ ፈጽሞ ስህተት ነው” ብለዋል።
እንዲህ አይነት ቀውስ ሲኖር መታወጅ ያለበት በፌደራል መንግስት በኩል የፌደራል የአደጋ ስጋት አመራር ምክር ቤት በኩል ያሉት ዶ/ር ለገሰ፤ ይህም ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ማእከል በማድረግ ተገምግሞ እንደሆነም አስታውቀዋል።
የፌደራል የአደጋ ስጋት አመራር ምክር ቤት በትግራይ ክልል 4 ዞኖች ድርቅ መከሰቱን ቢያረጋግጥም ከ77ቱ ድርቅና ረሃብ ጋር ይስተካከላል የሚል መረጃ እስካሁን እንዳላወጣም ሚኒስቱ ገልጸዋል።
ዓለም አቀፋ አጋር አካላት እርዳታ ባቆሙበት ሰዓትም መንግስት ፕሮጄክቶቹን አጥፎ ለትግራይ ክልል በበቂ ሁኔታ እርዳታ እያቀረበ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ዶ/ር ለገሰ አክለውም፤ “በ100 ሺህ የሚቆጠር ታጣቂ በባለሙያ ስም በአንድ ቦታ ሰብስቦ ለማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በተመደበ በጀት እየቀለቡ በምን ሞራል ነው ስለ ትግራይ ህዝብ ስቃይ ማውራት የሚችለው?” ሲሉም ጠይቀዋል።
በህዝብ ሽፋን የሚደረግ የትኛውም አይነት ፕሮፓጋንዳ ተቀባይነት እንደሌለውም የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በሀገሪቱ ስለ ተከሰተው ድርቅ በሰጡት መግለጫም አማራ ክልል 8 ዞኖች ፣ ትግራይ 4 ዞኖች፣ አፋር 3 ዞኖች እንዲሁም በሌሎች ክልልች የተለያዩ ኪስ ቦታዎች 3.8 ሚሊየን ዜጎች ከፍተኛ የድርቅ አደጋ መጋለጣቸውን አስታውቀዋል።
በጎርፍ አደጋም በሶማሌ ክልል በሸበሌ አፍዴርና ሊበን ዞኖች፣ በደቢብ ኢትዮጵያ ክልል፤ በደቡብ ኦሞ ዞን አና ዳሰነች ወረዳ፣ በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ጉጂ፣ ባሌ እና ምስራቅ ባሌ፤ በአማራ ክልል ምእራብ ጎጃም እና ማእከላዊ ጎንደር፤ በጋምቤላ ክልለ አኝዋ፣ ኢታንግ ልዩ ወረዳ እና ጋምቤላ ከተማ እንዲሁም በአፋር እና በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ጉዳት መድረሱን አስታውቀዋል።
በጎርድ አደጋውም ከ1.5 ሚሊየን በላይ ዜጎች መጎዳታቸውን ያስታወቁት ሚኒስትሩ፤ 125 ሺህ ሄክታር የእርሻ መሬት እና 123 ሺህ የግጦሽ መሬት ወድሟል፤ ከ21 ሺህ በላይ የእነሰሳት ሞት አስከትሏል ብለዋል።
መንግስት በድርቅና በጎርፍ ለተጎዱ አካባቢዎች ከሳለፍነው ዓመት ሐምሌ ው ጀምሮ 1 ሚሊየን 725 ሺህ ኩንታል በላይ የእርዳታ እህል ማቅረቡን እና ይህም 15.2 ቢሊየን ብር እንደሚገመት አስታውቀዋል።