ስምምነቱን መሉበመሉ ለመፈጸም ብዙ ይቀረናል-የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር
የፌደራል መንግስት በትናንትናው እለት ባወጣው መግለጫ በስምምነቱ አፈጻጸሙ ጉዳይ ትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደሩ ወቅሷል
ነገርግን አቶ ጌታቸው በስምምነቱ መሰረት በፌደራል መንግስት በኩል ያልተፈጸሙ በርካታ ነጥቦችን አንስተዋል
የፕሪቶሪያውን ስምምነት በመሉ ለመፈጸም ብዙ እንደሚቀር የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ ተናገሩ።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ ከክልላዊው ድምጸ ወያኔ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት የቋጨውን የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት "ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም ብዙ ይቀረናል" ብለዋል።
የፌደራል መንግስት በትናንትናው እለት ባወጣው መግለጫ በስምምነቱ አፈጻጸሙ ጉዳይ ትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደሩ ወቅሷል።
ነገርግን አቶ ጌታቸው በስምምነቱ መሰረት በፌደራል መንግስት በኩል አልተፈጸሙም ያሏቸውን በርካታ ነጥቦች አንስተዋል።
አቶ ጌታቸው የግጭት መቆሙ፣ የህወሓት ከሽብርተኝነት መዝገብ መሰረዝ እና የበጀት መለቀቅ በስምምነቱ የታዩ መሻሻሎች እንደሆኑ ገልጸዋል።
መሻሻሎች መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ ጌታቸው አልተፈጸሙም ያሏቸውን በርካታ ነጥቦች ዘርዝረዋል።
በጦርነቱ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደቀያቸው አለመመለስ፣ በአማራ ኃይሎች የተያዙት አወዛጋቢ የተባሉት ቦታዎች ወይም ምዕራብ ትግራይ እና ደቡብ ትግራይ ወደነበሩበት አለመመለስ እና የኤርትራ ኃይሎች የተወሰኑ የትግራይ ግዛቶችን ይዘው መቆየታቸው ስምምነቱ የተፈለገው ደረጃ ደርሷል ለማለት እንደሚያስቸግር አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።
የፌደራል መንግስት አወዛጋቢ ቦታዎችን በስሩ በማድረግ በህገ መንግስቱ መሰረት መፍትሄ ለመስጠት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ቢገልጽም አቶ ጌታቸው ይህን አይቀበሉትም።
አቶ ጌታቸው እንዳሉት ቦታዎች ከጦርነቱ በፊት ወደነበሩበት ወደ ትግራይ መካለል እንዳለባቸው እና ምርጫም ሆነ ህዝበ ውሳኔ ለማድረግ በጊዜያዊ ሳይሆን በተመረጠ የትግራይ ክልል መንግስት የሚከወን መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።
የፌደራል መንግስት ስምምነቱን ለመፈጸም ረጅም ርቀት ቢሄድም፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ "እግር የመጎተት አዝማሚያ" እያሳየ ነው የሚል ትችት ማቅረቡ ይታወሳል።
በመንግስት የሚነሳው ትጥቅ የመፍታት እና የመቀላቀል ጉዳይ በበጀት እጥረት ምክንያት የተፈለገውን ያህል አለመሄዱን የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ ለዚህ ግን ጊዜያዊ አስተዳደሩ ብቻ አይወቀስም ብለዋል።
የኤርትራ መንግስት በትግራይ ክልል የተወሰኑ ቦታዎችን እንደያዘ ክስ ቢቀርብበትም እስካሁን ቀጥተኛ መልስ አልሰጠም።