ትግራይ ከ1977ቱ ወደ ከፋ ረሀብ ልትገባ ጫፍ ላይ መድረሷን ጊዜያዊ አስተዳደሩ አስታወቀ
ጊዜያዊ አስተዳደሩ "90 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ለረሀብ እና ለሞት ተጋለጭ ሆኗል" ብሏል
ጊዜያዊ አስተዳደሩ የፌደራል መንግስት እና አለምአቀፍ ተቋማት እያንዣበበ ያለው የረሀብ እና የሞት አደጋ ለማስቀረት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቋል
ትግራይ ከ1977ቱ ወደ ከፋ የሀረብ አደጋ ልትገባ ጫፍ ላይ መድረሷን ጊዜያዊ አስተዳደሩ አስታወቀ።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ በፌስቡክ ገጻቸው የለጠፉት የጊዜያዊ አስተዳዳሩ ፕሬዝደንት ጽ/ቤት መግለጫ እንዳስታወቀው ትግራይ የረሀብ አደጋ አንዣቦባታል።
ጊዜያዊ አስተዳዳሩ እንደገለጸው ትግራይ በመላው ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጉዳት ካስከተለው በደርግ ዘመነ መንግስት ከተከሰተው የ1977ቱ ርሃብ ወደ ከፋ የረሀብ አደጋ ውስጥ ልትገባ ጫፍ ላይ ደርሳለች።
በትግራይ የነበረው አውዳሚ የጦርነት አሻራ እና ድርቅ ያስከተለው ረሀብ አደጋኛ ጥምረት መፍጠራቸውን የገለጸው ጊዜያዊ አስተዳደሩ "90 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ለረሀብ እና ለሞት ተጋለጭ ሆኗል" ብሏል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ በዚህ መግለጫው በጦርነቱ ወቅት የትግራይ የኢኮኖሚ መሰረት መድቀቅ፣ የጤና ተቋማት መውደም እና ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆን ህዝብ መፈናቀል፣ በትግራይ ብዙዎች ድህነትን መቋቋም እንዳይችሉ አድርጓቸዋል ሲል ገልጿል።
ጊዜያዊ አስተዳዳሩ እንደገለጸው የዝናብ እጥረት፣ የአንበጣ መንጋ መከሰት እና የሰብአዊ እርዳታ መቋረጥ በክልሉ ያለውን ችግር አባብሶታል።
የሰብአዊ እርዳታው እንደገና ቢጀመርም፣ ከሚፈለገው አንጻር ሲታይ በጣም ጥቂት የሚባል ነው ብሏል ጊዜያዊ አስተዳደሩ።
ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ብዙዎች በምግብ እጥረት ሞተዋል ያለው ጊዜያዊ አስተዳደሩ ህጻናት፣ አዛውንቶች እና ነፍሰጡሮች በረሀብ ሲሸነፉ የሚያሳይ ዘግናኝ መረጃ እያለ በቂ የሚባል ትኩረት አለማግኘቱን ገልጿል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይህን አደጋ ለመቀልበስ የገንዘብ አቅም እንደሌለው ገልጾ፣ የፌደራል መንግስት እና አለምአቀፍ ተቋማት እያንዣበበ ያለው የረሀብ እና የሞት አደጋ ለማስቀረት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንደገለጸው ችግሩ የማይፈታ ከሆነ ሀገራዊ እና ቀጣናዊ ሰላም እና መረጋጋትን ሊያውክ ይችላል።
የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት እና በፌደራል መንግስት መካከል ለሁለት አመት የዘለቀው ደም አፋሳሽ ጦርነት ህዳር 2015 ዓ.ም በፕሪቶሪያ በተፈረመው የዘላቂ ተኩስ አቀም ስምምነት ተቋጭቷል።
ስምምነቱን ወደ ተግባር በመቀየር ግን ክፍተቶች እንዳሉ በሁለቱም ወገኖች ይነሳሉ።
የፌደራል መንግስት ስምምነቱ የተፈረመበትን አንደኛ አመት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ መንግስት ስምምነቱን መሉ በመሉ ተግባራዊ ለማድረግ ቢሰራም በጊዜያዊ አስተዳደሩ በኩል "እግር የመጎተት አዝማሚያ ይታያል" የሚል ወቀሳ ማቅረቡ ይታወሳል።
መንግስት እንደገለጸው በስምምነቱ መሰረት በጊዜያዊ አስተዳደሩ የመወከል መብት ቢኖረውም፣ መተማመን እንዲፈጠር በማስብ ሳይሳተፍ ቀርቷል።
የህወሓት ታጣቂዎችን ትጥቅ አለመፍታትን መንግሰት ዋና ክፍተት አደርጎ አንስቶታል።
ይህን ተከትሎ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ ከክልላዊው ድምጸ ወያኔ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የትጥቅ መፍታት ጉዳይ በተጠበቀው ልክ ያልሄደው በበጀት እጥረት ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
አቶ ጌታቸው መንግስት ሊፈጽማቸው ሲገባ አልፈጸማቸውም ያሏቸውን ነጥቦችን አንስተዋል።
የውጭ ኃይሎችን ከትግራይ ክልል ይዞታዎች ማስወጣት እና በጦርነቱ የተፈናቀሉትን ወደ ቀያቸው መመለስ አልቻለም ሲሉ አቶ ጌታቸው መንግስትን ተችተው ነበር።
አሁን ላይ የስምምነቱ አፈጻጸም ምን ደረጃ ላይ እንዳለ አይታወቅም።