ባለ ገመድ መወጠሪያ ያለው ድልድዩ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል
የባህርዳር ከተማ ታላቅ መለያ ምልክት እንዲሆን የተገነባው የአባይ ወንዝ ድልድይ በዛሬው እለት ተመርቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ከክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ጋር በመሆን ከአራት አመት ተኩል በፊት ግንባታው የተጀመረውን የአባይ ድልድይን ዛሬ መርቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የድለድዩን መመረቅ አስመልከቶ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ “በባህርዳር ከተማ የተመረቀው የአባይ ድልድይ በሰዎች መካከል ያለን ግንኙነት በማጠናከር እና የንግድ እድሎችን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ርምጃ ነው” ብለዋል።
“ከግዘፋዊ ቁሳዊ መዋቀሩ ባሻገርም ልዩነቶችን የማጥበብ፤ በተቃራኒ ጎራ ላሉ ሰዎች መገናኛ ድልድዮችን የማነፅ ርዕያችን መዘርጊያ ምልክት ነው” ሲሉም ገልጸዋል።
የአባይ ድልድይ እውነታዎች
አዲስ የአባይ ድልድይ የ380 ሜትር ርዝመት ያለው በሁለቱም የመንገድ ክፍል ባለሶስት መስመር የተሽከርካሪ መንገድን ብሎም በጎን የብስክሌት መጋለቢያ መስመር የተሰናዳለት ድልድይ ነው።
የአባይ ወንዝ ድልድይ በጥቅሉ 43 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ሲሆን በግራና በቀኝ በአንድ ግዜ 6 ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚችል ይሆናል።
አንዱ መስመር ብቻ 21.5 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን በውስጡ ባለ ሶስት መስመር የተሸከርካሪ መሄጃ ፣ የብስክሌት ተጠቃሚዎች መስመር እንዲሁም 5 ሜትር የእግረኛ መሄጃን ያካቷል።
ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ዘመናዊ ድልድዩ፤ በጣም ውስብስብ ገመድ መወጠሪያ ያለው ዘመናዊ ድልድይ ነው።
ድልድዩ ከፊትና ከሁዋላ ከግራና ከቀኝ በ18 ኬብሎች በአጠቃላይ በ72 ኬብሎች (በገመዶች የተወጠረ) ሆኖ ጠቅላላ ክብደቱ በገመዶቹ አማካይነት ወደ ቋሚው ምሰሶ የሚተላለፍና ከምሰሶውም ወደ መሰረቱ የሚዘልቅ ነው።
ከነባሩ አባይ ድልድይ ማለትም ባህርዳር ከተማ ውስጥ ከሚገኘው 2 ኪ.ሜ እርቀት ላይ የተገነባው አዲሱ የአባይ ወንዝ ድልድይ በዘመናዊነቱም እንዲሁም ማራኪነቱም በሀገራችን ግንባር ቀደም ነው ተብሏል።
የባህርዳር ከተማ ታላቅ መለያ ምልክት እንዲሆን የተገነባው የአባይ ወንዝ ድልድይ የአካባቢውን የኢኮኖሚ እድገት ብሎም የመገናኛ አውታር የሚያነቃቃ ይሆናል።