የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሹመት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ አስነሳ
ጌዲዮን ጢሞቲዮስ የዲፕሎማሲ እውቀት እና ልምድ የላቸውም የሚለው ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል ነበር
ሚኒስትሩ የፍትህ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ያመጡት ለውጥ የለም በሚል ጥያቄ ተነስቶባቸዋል
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሹመት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ አስነሳ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ የአምስት ሚኒስትሮችን ሹመት ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ውሳኔ አሳልፏል።
ለምክር ቤቱ ከቀረቡ አጀንዳዎች መካከል የአምስት ሚኒስትሮች ሹመት አንዱ ሲሆን የምክር ቤት አባላት እና የመንግስት ተጠሪ ክርክር አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ከሁለት ሳምንታት በፊት የሾሟቸው አምስት ሚንስትሮች በዛሬው የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ የቀረበ ሲሆን የምክር ቤት አባላት በሹመቱ ዙሪያ ጥያቄ አንስተዋል።
ከተነሱ ጥያቄዎች መካከልም የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ተደርገው የተሾሙት እና ስራ የጀመሩት ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) አንዱ ነበር።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ወክለው የምክር ቤቱ አባል የሆኑት ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ጥያቄ ካነሱት መካከል አንዱ ነበሩ።
ሹመቱን አስመልክቶ ካነሱት ጥያቄ መካከልም "የፍትህ ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ ለውጥ ያመጣሉ ተብለው ተስፋ ተጥሎባቸው የነበረ ቢሆንም የፍትህ ዘርፉን ለፖለቲካ ጥቅም እንዲውል ፈቅደዋል፣ ህግ በይፋ ሲጣስ ዝም ብለዋል አልያም ተባብረዋል" ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም "የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት ሲጠይቅ የነበረውን የፍትህ ጥማት ከማርካት ይልቅ ፍትህ የፖለቲካ መሳሪያ እንዲሆን አድርገዋል፣ ከዚህ አንጻር ያላቸው አፈጻጸም ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት የሚያበቃቸው አይደለም" የሚለው በምክር ቤት አባሉ ተነስቷል።
ሌላኛው የምክር ቤቱ አባል ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ በበኩላቸው የሚኒስትሮች ሹሙት ለተሿሚዎች ከመሰጠቱ በፊት ሹመታቸው እንዲጸድቅ ለምን ለምክር ቤቱ አይቀርብም? ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል።
ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት የቀረቡት ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ያላቸው ስራ ለምድ ዘርፉ የሚጠይቀውን የዲፕሎማሲ እውቀት ስለመያዛቸው መንግሥት ማብራሪያ እንዲሰጥም ካሚል ሸምሱ ጠይቀዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ የሆኑት ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።
ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በምላሻቸው መንግሥት እና ገዢው ፓርቲ ብልጽግና ስራዎችን የሚገመግምበት የራሱ መድረክ እንዳለው እና ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ከዚህ በፊት በሰሩባቸው ተቋማት ውስጥ ለውጥ ያመጡ ስኬታማ አመራር መሆናቸውን ተናግረዋል።
መንግሥት ሹመቱን ለተሿሚዎች ከመስጠቱ በፊት ለምን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ አላጸደቀም? በሚል ለተነሳው ጥያቄ "ወቅቱ የክረምት ወቅት በመሆኑ፣ የምክር ቤት አባላትም ወደ ተመረጡባቸው አካባቢዎች በመሄዳቸው እና ተቋማትን ለህዝብ ጥቅም ሲባል ያለ አመራር ማቆየት የህዝብን እና ሀገርን ጥቅም ይጎዳል በሚል ምክንያት ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ምክር ቤቱ ከጥያቄ እና መልስ በኋላ የጌዲዮን ጢሞቲዮስን ጨምሮ የአምስት ሚኒስትሮችን ሹመት በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል።