“ህወሓት ወራሪ እንጂ ተጎጂ አይደለም”- ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በጉባዔው መክፈቻ ትናንት ንግግር ማድረጋቸው የሚታወስ ነው
ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ በ48ኛው የዓለም ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ላይ በመሳተፍ ላይ ናቸው
የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ወቅታዊ የኢትዮጵያን ሁኔታን የተመለከተ ማብራሪያን በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ለተሰባሰቡ የአፍሪካ አምባሳደሮች እየሰጡ ነው፡፡
ዶ/ር ጌዲዮን ትናንት በጄኔቫ በተጀመረው 48ኛው የዓለም ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ላይ ማብራሪያን ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸው “ህወሓት ወራሪ እንጂ ተጎጂ አይደለም” ሲሉ ነው ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ የተናገሩት፡፡
በጉባዔው የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብት ሁኔታዎችን በተመለከተ ውይይት ተደርጓል፡፡
በውይይቱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)ም ንግግር አድርገዋል፡፡
በንግግራቸው ከትግራይ ግጭት ጋር በተያያዘ ተፈጽመዋል የተባሉ ዐይነተ ብዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የምርመራ ሂደት ገና አለመጠናቀቁን ያስታወሱ ሲሆን አሁን ላይ ሆኖ ድምዳሜዎችን ከመስጠት መቆጠብ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ተፈጽመዋል በሚል የሚናፈሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ታሪኮችን ውስብስብነት በውል መረዳት እንደሚያስፈልግም ነው ዶ/ር ዳንኤል የተናገሩት፡፡
“ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ገንቢ ሚናን”ሊጫወት እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት፡፡
የዓለም ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የምክር ቤት አባላት “የወገኑን ሰቆቃ ለማብቃት የሚያስችለው የችግሩ መፍቻ ቁልፍ አሁንም በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ” የሚገኝ መሆኑን ልብ ሊያደርጉ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ጥሰቶቹን ለመፍታት የሚያስችል “ትህትና” እንደሚያስፈልግና ዓለም አቀፍ አጋሮችን ጨምሮ ሁሉም አካላት ይህንኑ ሊላበሱ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ጉባዔው እስከ መጪው መስከረም 28 ድረስ እንደሚዘልቅ ከኮሚሽኑ የተገኙ መረጃዎች አመልከተዋል፡፡