ምክር ቤቱ ለ6 ወራት ታውጆ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጀ አነሳ
መንግስት ጥቅምት 24፣2014 ለ6 ወራት የሚቆይ የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ ነበር
ምክር ቤቱ አዋጁን በ63 ተቃውሞ በ21 ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ እንዲነሳ ወስኗል
የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሃገሪቱ ለ6 ወራት ተጥሎ የቆየውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አነሳ።
ምክር ቤቱ በዛሬው እለት ባካሄደው ስብሰባው፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲያበቃ ያቀረበለት የውሳኔ ሀሳብ ላይ ተወያይቷል።
ምክር ቤቱ በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ከተወያየ በኋላ በመላ ሀገሪቱ ለ6 ወራ ታውጆ የነበረው የአስቸኳይ ጊዝ አዋጅ በ63 ተቃውሞ በ21 ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ እንዲነሳ ወስኗል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ጋር ተያይዞ ያላጠናቀቃቸው ጅምር ስራዎች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንዲያጠናቅቅ እንዲሁም የፍትህ አካላትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ጋር ተያይዞ የጀመሯቸውን ጉዳዮች በመደበኛው የፍትህ አሰሰጣጥ ስርአት እንዲያጠናቅቁም ምክር ቤቱ ወስኗል።
የኢትየጵያ መንግስት ህወሃት በሀገር ህልውና ሉአላዊነት ላይ ደቅኖታል ያለውም ስጋት ለመቀልስ ጥቅምት 24፣2014 የጣለውን ለስድስት ወራት የሚቆይ የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ ነበር።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባሳለፍነው ጥር 18 2014 ባካሄደው ስብሰበዋው የአዋጁ ጊዜው ሳይደርስ ቀደም ብሎ እንዲነሳ ውሳኔ አሳልፎ ነበር።
አዋጁን ማውጣት አስፈላጊ የነበረበት ሁኔታ አሁን ላይ ስለተቀየረ እና ስጋቱን በመደበኛ የህግ ማስከበር ስራ መከላከል ስለሚቻል ለስደስት ወራት የታወጀውን አዋጅ ተፈጻሚ የሚሆንበት ጊዜ ማሳጠር አስፈላጊ መሆኑንም ነው ምክር ቤቱ የገለፀው።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሔደው 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባው በሀገር ህልውና ሉአላዊነት ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመከላከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ መወሰኑ ይታወሳል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ጥቅምት 24 ቀን 2014 ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባው የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ ተቀብሎ በመላ ሀገሪቱ ለ6 ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዝ አዋጄ አውጆ ነበር።
የአስቸኳ ጊዜ አዋጁ የታወጀው በሀገር የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ ከፍተኛ አደጋ በመደቀኑና፤ ይህንንም አደጋ በመደበኛ ሁኔታ መቆጣጠር ባለመቻሉ የጸጥታና የደህንነት ተቋማትንና ዜጎችን በማቀናጀት አደጋውን ለመቀልበስ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖር ለማድረግ እንደሆነም በወቅቱ ተገልጿል።