ዓረና፤ በሀገራዊ ምክክሩ “ህወሃት እና ኦነግ ሸኔ ካልተሳተፉ ዋጋ የለውም” አለ
ትጥቅ ያነሱ ቡድች ሁሉ በምክክሩ ላይ መሳተፍ እንዳለባቸውም ፓርቲው ጠይቋል
ህወሃትን ከሽብርተኝነት ዝርዝር ማንሳት እንደሚቻል ገልጸዋል
ዓረና፤ በሀገራዊ ምክክሩ “ህወሃት እና ኦነግ “ሸኔ” ካልተሳተፉ “ዋጋ የለውም” አለ።
በኢትዮጵያ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ሀገራዊ ምክክር ላይ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች መሳተፍ አለባቸው ብሎ እንደሚያምን ዓረና ትግራይ ለሉዓላዊለነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አስታወቀ።
የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ጎይቶም ጸጋዬ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሀገራዊ ምክክሩ ትጥቅ ያነገቡ ቡድኖችን ጭምር ማካተት እንዳለበት ተናግረዋል።
ምክክር ኮሚሽኑ ምን መሆን እንደነበረበትና እንዳለበት ቀደም ባሉት ዓመታት ጭምር እንደገለጸ ያስታወቀው ፓርቲው አሁን በሚደረገው ምክክር ሁሉም ወገኖች መካተት እንዳለባቸው አሳስቧል።
ፓርቲው፤ ህወሃት እና ኦነግ ሸኔን ጨምሮ ሌሎች ትጥቅ ያነሱ ኃይሎች በሙሉ በሀገራዊ ምክክሩ ላይ ካልተሳተፉ የሚደረገው ውይይትም ሆነ ምክክር ዋጋ አይኖረውም ብሏል።
በምክክሩ፤ መንግስት “ኦነግ ሼኔ “የሚለውን ቡድን ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ያሉ ታጣቂዎችን፣ ኦብነግን፣ ኦፌኮን ሌሎች ጨምሮ ሁሉም መሳተፍ እንዳለባቸው ያነሱት አቶ ጎይቶም፣ በትግራይ ክልልም በተመሳሳይ ሁሉም ኃይሎች መሳተፍ አለባቸው ነው ያሉት።
ህወሃት በሽብር የተፈረጀ ቡድን መሆኑን ተከትሎ በምክክሩ አይሳተፍም በሚል የተለያዩ ሃሳቦች ቢቀርቡም የዓረና ምክትል ፕሬዝዳንት ግን “እኛ ከአሁን በፊትም ሽብርተኛ ተብለው የነበሩት ግንቦት ሰባት፣ አርበኞች፣ ኦነግ፣ ዴሚሂት እና ሌሎችም በውይይት እንዲሳተፉ ስንጠይቅ ነበር፤ ስለዚህ ይህ የህወሃት ጉዳይ ለእኛ አዲስ ጉዳይ አይደለም፤ ህወሃትን ከሽብር ዝርዝር ማንሳት ይቻላል” ሲሉ መልሰዋል፡፡
በሌሎች ሀገራት መንግስት ከአሸባሪዎች ጋር እንደሚደራደር በአብነት ያነሱት አቶ ጎይቶም፤ ሀገራትና መንግስታት እንኳን መንግስት ሆኖ ከቆየው ህወሃት ጋር ይቅርና ለተወሰኑ ዜጎቻቸው ሲሉ ከተራ ሽፍቶች ጋርም እንደሚደራደሩ ለአብነት አንስተዋል አቶ ጎይቶም፡፡
አቶ ጎይቶም፤ አሁን ላይ ከየትኛውም ነገር በፊት ተኩስ ማቆም፣ መፈናቀሎችን ማስቀረት፤ ተፈናቃዮችን ወደቀያቸው መመለስና አገልግሎቶችን ማስጀመር ሊቀድም ይገባል ብለዋል፡፡
መንግስት በሽብር የፈረጀው ህወሃት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል ከፌዴራል መንግስት ጋር ንግግር መጀመሩን መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን መንግስትም “እስካሁን በይፋ የተጀመረ ድርድር የለም፤ ይህ ማለት ግን ድርድር አይደረግም ማለት አይደለም” ማለቱን ተከትሎ አል ዐይን አማርኛ ይህንን ጉዳይ ዓረና እንዴት ይመለከተዋል የሚል ጥያቄ አቅርቧል፡፡
የዓረና ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ጎይቶም፤ ድርድርን በተመለከተ የፌዴራል መንግስት እና ሕወሃት ከሚሰጡት መግለጫ ውጭ ምንም አይነት መረጃ እንደሌላቸው አንሰተዋል፡፡ ዓረና ሁሉም ኃይሎች ከጦርነት በፊት ወደነበሩበት ቦታ መመለስ አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ይህም ማለት “የአማራ ኃይሎች” ከ “ምዕራብ ትግራይ” “የትግራይ ኃይሎች” ከአፋር እና ከአማራ ክልል መውጣት አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የፌዴራል መንግስት እና ሕወሃት እርስ በእርስ ከመካሰስ እና ከመወቃቀስ ወጥተው ዕርዳታ እንዲገባ አሁን ያለው ታሪካዊ ስህተት መሆኑን ማመን እንዳለባቸው አቶ ጎይቶም ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሀገራዊ ምክክሩ ላይ የትግራይ ሕዝብ “ይወክሉኛል” በሚላቸው ቡድኖች መሳተፍ እንደሚችል መግለጻቸውን ይታወሳል፡፡ ዓረና በበኩሉ ሁሉም አካላት በምክክሩ መሳተፍ አለባቸው ብለዋል አቶ ጎይቶም።