የቶኪዮ ኦሎምፒክ ሻምፒዮኑ ሰለሞን ባረገ በነገው እለት በሚካሄደው የ10 ሺህ ሜትር ፍጻሜ ይጠበቃል
የጂምናስቲክ፣ እግርኳስና ሌሎች ስፖርታዊ ውድድሮችን ሲያካሂድ የሰነበተው የፓሪስ ኦሎምፒክ ዛሬ የአትሌቲክስ ውድድሮችን አስጀምሯል።
ኢትዮጵያ በተሳተፈችበት የ20 ኪሎሜትር ወንዶች የእርምጃ ውድድር አትሌት ምስጋና ዋቁማ 6ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
ነገ ምሽት 4 ስአት ከ20 የሚካሄደው የ10 ሺህ ሜትር ወንዶች ፍጻሜ ኢትዮጵያ በፓሪስ ቀዳሚውን የወርቅ ሜዳልያ የምታገኝበት እንዲሆን የበርካቶች ምኞት ነው።
ከአራት አመት በፊት በጃፓን መዲና ቶኪዮ በተካሄደው ኦሎምፒክ በርቀቱ ለሀገሩ የወርቅ ሜዳልያ ያስገኘው አትሌት ሰለሞን ባረጋ ለሁለተኛ የኦሎምፒክ ድል ይጠበቃል።
ቅዳሜ ሀምሌ 29 2016 ደግሞ የ5 ሺህ ሜትር ፍጻሜ ሲደረግ የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳልያን ከማግኘት ባለፈ የርቀቱን ሪከርድ ለማሻሻል ተዘጋጅቻለሁ ያለችው አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ ትጠበቃለች።
አትሌት ጉዳፍ በ5 ሺህ ሜትር እና 1 ሺህ 500 ሜትር ሀገሯን ወክላ ትሳተፋለች።
ኢትዮጵያ በወንዶችም ሆነ በሴቶች በፓሪስ ከምትጠበቅባቸው ውድድሮች መካከል የማራቶን ውድድር ቀዳሚው ነው።
በወንዶች የኦሎምፒክ ሻምፒዮኑ ቀነኒሳ በቀለ፤ በሴቶች ደግሞ የርቀቱን ክብረወሰን ባለፈው አመት በበርሊን የያዘችው ትዕግስት አሰፋ ተጠባቂ ናቸው።