በፓሪስ ኦሎምፒክ ደቡብ ሱዳናውያንን ያበሳጨው ክስተት ምንድን ነው?
የፓሪስ ኦሎምፒክ አዘጋጆች በደቡብ ሱዳን ጨዋታ ላይ የሱዳንን ብሄራዊ መዝሙር ከፍተዋል
የደቡብ ሱዳን የቅርጫት ኳስ ተጫዋቾቹ ሁኔታውን “ክብረ ነክ” ሲሉ ገልጸውታል
የፓሪስ ኦሎምፒክ አዘጋጆች በደቡብ ሱዳን የቅርጫት ኳስ ጨዋታ መክፈቻ ላይ የተሳሳተ ብሄራዊ መዝሙር መክፈታቸው ደቡብ ሱዳናውያንን አበሳጭቷል።
የኦሎምፒክ አዘጋጆች ደቡብ ሱዳን ከፖርቴሪኮ ጋር በነበራት የቅርጫት ኳስ ጨዋታ መጀመሪያ ላይ በደቡብ ሱዳን ፋንታ የሱዳንን ብሄራዊ መዝሙር መክፈታቸው ነው የተነገረው።
ባሳለፍነው እሁድ በፔሪ ማውሪ ስታዲየም የተካሄደውን ጨዋታ ለመታደም የገቡ ተመልካቾች በደቡብ ሱዳን ብሄራዊ መዝሙር ፋንታ የሱዳን ብሄራዊ መዝሙር በመከፈቱ በጩኸት ተቃውሞዋቸወን አሰምተዋል።
የተመልካቾችን የተቃውሞ ድምጽ ተከትሎ በስህተት የተከፈተው መዝሙር ወዲያዉኑ ቆሞ ከ3 ደቂቃ ቆይታ በኋላ እንዲስተካከል መደረጉ ታውቋል።
የደቡብ ሱዳን የቅርጫት ኳስ ተጫዋች በበኩሉ ሁኔታውን “ክብረ ነክ” ነው ሲል የገለጸው ሲሆን፤ “ይህ ትልቅ መድረክ ነው፤ አዘጋጆቹ የበለጠ አውቀት ሊኖራቸው ይገባል” ብሏል።
የፓሪስ ኦሎምፒክ አዘጋጆች ባወጡት መግለጫ ስህተቱ በሰው የተፈጠረ ስህተት መሆኑን ጠቅሰው ይቅርታ ጠይቀዋል።
የደቡብ ሱዳን የቅርጫት ኳስ ተጫዋቾች በጨዋታው መክፈቻ ላይ በተሳሳተ ብሄራዊ መዝሙር ቢበሳጩም በጨዋታው ፖርቴሪኮን 90 ለ 79 በሆነ ውጤት በመርታት አዲስ ታሪክ አስመዝግበዋል።
የፓሪስ ኦሎምፒክ አዘጋጆች ከተጀመረ የቀናት እድሜ ባለው ኦሎምፒክ ላይ ስህተት ሰርተው ይቅርታ ሲጠይቁ ይህ ለሁለተኛ ጊዜያቸው ነው።
በውድድሩ መክፈቻ ላይ ተሳታፊ ሀገራት በሴን ወንዝ ላይ ሲያልፉ መድረክ መሪዎች ሀገራትን አሳስተው የጠሩ ሲሆን፤ በዚህም በእንግሊዝኛ እና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎች ደቡብ ኮሪያን እንደሰሜን ኮሪያ መጥራታቸው ቁጣን መቀስቀሱ ይታወሳል።
ክስተቱ የተፈጠረው የደቡብ ኮሪያ አትሌቶች ሰንደቅ አላማቸውን ይዘው እያለፉ እና እያውለበለቡ እያለ በስህተት ሰሜን ኮሪያ ተብለው ተጠርተዋል።
ደቡብ ኮሪያዊያን በስህተት መጠራታቸው እንዳበሳጫቸው በመንግስታቸው በኩል እና በማህበራዊ ትስስር ገጾች ተናግረዋል።
የፓሪስ ኦሎምፒክ አዘጋጆች እና ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ በበኩላቸው ለተፈጠረው ስህተት በኮሪያ ቋንቋ ይቅርታ ጠይቀው ስህተት እንደማይደገም አስታውቀዋል።