የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በ6 ወራ ውስጥ 205 ሠራተኞቹ ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ
አገልግሎት በ6 ወር ውስጥ ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ፓስፖርት ታትሞ ወደሀገር ውስጥ በማስገባቱን አስታውቋል
ከመጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም በኋላ ዜጎች በተሰጣቸው የቀን ቀጠሮ መሰረት ፓስፖርታቸውን መረከብ ይችላሉ ተብሏል
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ባለፉት 6 ወራት ውስጥ 205 ሠራተኞቹ ላይ እንደየጥፋታቸው መጠን ከስራ እስከማገድ የሚደርስ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት የአገልግሎቱን የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ነው ይህንን ያሉት።
በዚህም አገለግግሉቱ በ6 ወር ውስጥ ከዋና ቢሮ፣ ከቅርንጫፍ ጽ/ቤት፣ ከቦሌ፣ ከኬላዎች በድምሩ 205 የሚሆኑ ሠራተኞች ላይ እርምጃ ወስዷል ብለዋል።
እርምጃ የተወሰደባቸው ሰራተኞች ውጭ ካሉ ደላሎች ጋር በመተባበርና የአሰራር ክፍተትን በመጠቀም ከህብረተሰቡ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሲሰሩ የነበሩና መሆናቸውንም ዳይሬክተሯ አስታውቀዋል።
በዚህም መረጃ የተገኘባቸውን ለህግ አካላት የማቅረብና እንደየጥፋታቸው ከስራ እንዲታገዱና የህግ ውሳኔ እንዲሰጣቸው መደረጉን ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ተናግረዋል።
ከፓስፖርት ጋር በተያያዘም “የደንበኞችን ጥያቄ ሙሉ ለሙሉ ለመመለስ በ6 ወር ውስጥ ከ1.1 ሚሊዮን በላይ የፓስፖርት ቡክሌት ወደሀገር አስገብተናል” ብለዋል።
በ6 ወራት ውስጥ ለአዲስ አበባ 260 ሺህ 371፣ በየአካባቢው ላሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች 269 ሺህ 358፣ በአስቸኳይ 35 ሺህ 394 እና በውጭ ለሚኖሩ ኢትዬጵያዊያን 81,416 በድምሩ 646 ሺህ 539 ፖስፖርት ታትሞ ማሰራጨት መቻሉን ገልፀዋል።
አሁን ላይ ምንም አይነት የተጠራቀመ ፍላጐት እንደሌለ የገለጹት ዳይሬክቷል፤ “ከመጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም በኋላ ዜጎች በተሰጣቸው የቀን ቀጠሮ መሰረት ፓስፖርታቸውን መረከብ ይችላሉ” ብለዋል።
አሁን ያለዉን የፓስፖርት ወደ ኢ-ፓስፖርት በመቀየር በሀገር ውስጥ እንዲመረት ውል በመያዝ የዲዛይን ስራዎች መጠናቀቁንና የግዥ ትዕዛዝ አልቆ ወደስራ የተገባ በመሆኑ በ1 አመት ጊዜ ውስጥ ወደ ኢ-ፖስፖርት የሚገባበት ሁኔታ የተመቻቸ መሆኑን ገልፀዋል።
ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት አክለውም፤ ሀሰተኛ ሰነድ በመጠቀም በሀገሪቱ በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የነበሩ የውጭ ዜጐችን አገልግሎቱ ጥሪ በማድረግ 10 ሺህ 467 የውጭ ዜጐች የተመዘገቡ መሆኑንና ወደህጋዊ መንገድ የማስገባት ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል።