የስልጣን ፍላጎት እና የተዛቡ ትርክቶች በኢትዮጵያ ለሚፈጠሩ አለመረጋጋቶች ዋነኛ ምክንያቶች እንደሆኑም ሚንስቴሩ አስታውቋል
የጸጥታ ችግሮች ለስራው እንቅፋት እንደሆነበት የሰላም ሚንስቴር አስታወቀ።
የሰላም ሚንስቴር የ2016 በጀት ዓመት የሶስት ወራት እቅድ አፈጻጸሙን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል።
የምክር ቤቱ አባላትም ኢትዮጵያ ለምን በግጭት አዙሪት ውስጥ ገባች? አሁን ያሉ ጦርነቶች አስቀድሞ ለምን ማስቆም አልተቻለም? የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን ለማሻሻል የሰላም ሚንስቴር ምን ሰራ? የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት አፈጻጸም ምን ላይ ነው? በኢትዮጵያ ዋነኛ የግጭት ምንጮችስ ተለይተዋል? እና ሌሎችንም ጥያቄዎች እንዲመለሱላቸው ጠይቀዋል።
ሚንስቴሩ ለምክር ቤቱ አባላት ባቀረበው ሪፖርት ላይ እንደገለጸው አሁን ላይ በኢትዮጵያ ከመኖሪያ ቤታቸው የተፈናቀሉ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ደርሷል ብሏል።
ተፈናቃዮቹን ወደ ቀድሞ ቤታቸው ለመመለስ እንደ ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም ) ካሉ ሌሎችም ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ሚንስቴሩ አስታውቋል።
የሰላም ሚንስቴር ዴዔታ አቶ ታዬ ደንደዓ በሰጡት ምላሽ በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ላሉ የጸጥታ ችግሮች የስልጣን ፍላጎት፣ የተዛቡ ትርክቶች፣ ስለ ሀገር ያለው አመለካከት የተዛባ መሆን ዋነኞቹ ምክንያቶች እንደሆኑ ተናግረዋል።
አቶ ታዬ አክለውም በኢትዮጵያ የጎሳ እና ብሄር ግጭቶች መቀነሳቸው፣ አሁን ላይ ያሉ የጸጥታ ችግሮች በብሄር እና ጎሳ መካከል ያሉ እንዳልሆኑም በምላሻቸው ላይ ገልጸዋል።
ሚንስቴሩ በኦሮሚያ እና ሶማሊ ክልሎች አዋሳኝ ዞኖች ላይ በተለይም ባቢሌ አካባቢ የተፈጠረው ግጭት እንዳይባባስ የህዝብ ለህዝብ እና አመራር ለአመራር ውይይት ማድረጉን እንዲሁም በጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ የነበሩ የጸጥታ ችግሮችን መፍታቱንም በሪፖርቱ ላይ አንስቷል።
አሁን በኦሮሚያ እና አማራ ክልል ያሉ የጽጥታ ችግሮች አስቀድመው ተለይተው እና ምላሽ የሚያስፈልጋቸው ተብለው ተለይተው እንደነበር የጠቀሱት አቶ ታዬ ችግሮቹን በውይይት ለመፍታት ጥረቶች እየተደረጉ እንደሆነም ተናግረዋል።
ይሁንና ሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉት የጸጥታ ችግሮች ያቀዳቸውን ስራዎች ለመፈጸም እንቅፋት እንደሆኑበት ገልጿል።
የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን እና የክልል ለክልል ግንኙነቶችን ለማሻሻል በአመራሮች ተደራራቢ ስራ እና ፍላጎት ማነስ ምክንያት መፈጸም አለመቻሉን ሚንስቴሩ አስታውቋል።