በቅርቡ የኢትዮጵያን ሜትር ታክሲ ገበያ የተቀላቀለው ያንጎ ምን አዲስ ነገር ይዟል?
መሰረቱን ሩሲያ ያደረገው ያንጎ በአፍሪካ 12ኛውን ቅርንጫፍ በኢትዮጵያ ከፍቷል
ኩባንያው አሽከርካሪዎችን ከመደጎም ባለፈ ብዙ ደንበኞች እንዲኖራቸው የሚያደርግ አሰራር ይዞ መምጣቱን አስታውቋል
በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ማስታወቂያው ደርቷል፡፡ ከዚህ ባለፈም በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ባሉ አደባባዮች ማስታወቂያውን ማየት ጀምረናል፡፡ አልፎ አልፎም በተሸከርካሪዎች ላይ ያንጎ የሚል ጽሁፍ ያለባቸው ተሽከርካሪዎች በከተማዋ ሲንቀሳቀሱ እየታየ ይገኛል፡፡
ደማቅ ቀይ ቀለምን መለያው አድርጎ የመጣው ይህ የሜትር ታክሲ ወይም ራይድ ኩባንያ ያንጎ ይባላል፡፡
ይቅናለም አበበ (ዶ/ር) የያንጎ ኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ አልዐይን ከስራ አስኪያጁ ጋር ስለ ያንጎ ምንነት፣ በኢትዮጵያ ስላለው እቅድ እና ሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርጓል፡፡
ስራ አስኪያጁ በዚህ ጊዜ እንዳሉት ድርጅታቸው ያንጎ አሽከርካሪዎችን እና ደንበኞችን ወይም ተሳፋሪዎችን የሚጠቅም አሰራር ይዞ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
ያንጎ የኢትዮጵያን ገበያ ከተቀላቀለ ገና አንድ ወሩ ነው ያሉት ስራ አስኪያጁ በሜትር ታክሲ ገበያ ለይ ዉጤታማ ለመሆን ግብ ሰንቀው ወደ ስራ መግባታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
ያንጎ በአዲስ አበባ የሜትር ታክሲ ገበያን የተቀላቀለው በውድድር ላይ የተመሰረተ እና ዘርፉን የበለጠ ማሻሻል የሚያስችሉ አሰራሮችን ዘርግቶ ነውም ብለዋል፡፡
የያንጎ ዋና መወዳደሪያ ምንድን ነው? በሚል ጥያቄ ላቀረብንላቸው ጥያቄም እኛ በዋናነት ይዘን የመጣነው አሽከርካሪዎች ብዙ መንገደኞችን እንዲያገኙ በማድረግ ከብዙ ስራ ብዙ ገቢ እንዲያገኙ ማድረግ ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
መንግስት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጥያቄን ውድቅ አደረገ
ከዚህ በተጨማሪም ተጠቃሚዎች የበለጠ ደህንነት እንዲሰማቸው የሚያደርጉ አሰራሮችን ይዘን መጥተናል ይህም የሜትር ታክሲን የበለጠ ውድድር ያለበት እንዲሆን ያደርጋልም ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከያንጎ ኩባንያ ጋር ለሚሰሩ አሽከርካሪዎች የቴክኒክ ስልጠና እንሰጣለን ለአብነትም የጎግል ማፕ እና ነዳጅ መቆጠብ የሚያስችሉ አሰራሮችን ለአሽከርካሪዎች እንደሚሰጡም ይቅናአለም ተናግረዋል፡፡
ሁሉም አሽከርካሪዎች ጎግል ማፕ የመጠቀም ክህሎት የሌላቸው መሆኑ፣ ሁሉም የትራንስፖርት ፈላጊዎችም ድጅታል እውቀታቸው እኩል አለመሆኑ እና ከዚህ በፊት የነበሩ ተለምዷዊ የሜትር ታክሲ አሰራሮች ለስራቸው ፈታኝ ሊሆንባቸው እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡
የንግድ ፈቃድ መያዝ፣ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ የተመረቱ ኮድ 3 እና ኮድ 1 ተሽከርካሪ ያላቸው አሽከርካሪዎች ወይም ባለንብረቶች ከያንጎ ጋር መስራት እንደሚችሉም ተገልጿል፡፡
ያንጎ አሁን ላይ ለተጠቃሚዎች በመነሻ ዋጋ 72 ብር አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን ይህም ሾፌሮችን ለመደጎም ደግሞ ሰዓቱ የሚሰላ ማለትም በስራ ሰዓት መግቢያ፣ መውጫ እና አዘቦት ጊዜ ከ130 ብር ጀምሮ እስከ 170 ብር ጀምሮ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሆነ ስራ አስኪያጁ ጠቅሰዋል፡፡
ደንበኞች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲጠቀሙ እንዲሁም አሽከርካሪዎች ደግሞ ነዳጅ መቆጠብ፣ እንደ ማፒንግ ያሉ መረጃዎችን እንዲያገኙ በማድረግ እና አሽከርካሪዎች ብዙ ደንበኞች እንዲያገኙ በማድረግ መወዳደር ዋናው አላማችን ነውም ብለዋል፡፡
የተለያዩ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባትም በየጊዜው የዋጋ ማስተካከያ ይደረጋል ያሉት ይቅናአለም አበበ (ዶ/ር) ኮምፎርት፣ ኢኮኖሚ እና መሰል አሰራሮችን እንደሚከተሉም ተናግረዋል፡፡
አገልግሎቱን አሁን ላይ በአዲስ አበባ ጀመርን እንጂ ቀስ በቀስ ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች የማስፋት እቅድ እንዳላቸውም ይቅናአለም አበበ ተናግረዋል፡፡
ያንጎ የራይድ ኩባንያ በፈረንጆቹ 1997 ጀምሮ መሰረቱን ሩሲያ እና ኔዘርላንድ በማድረግ በአውሮፓ፣ እስያ ፣አፍሪካ እና ደቡብ አሜሪካ እየተስፋፋ ያለ ተቋም ነው፡፡
በአፍሪካም ኮቲዲቯር፣ ጋና፣ ካሜሩን፣ ሴኔጋል፣ ዛሚቢያ፣ አንጎላ፣ ኮንጎ ብራዛቪል፣ ሞዛምቢክ፣ አልጀሪያ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ሞሮኮ በመስራት ላይ ሲሆን ከአንድ ወር በፊት ደግሞ በኢትዮጵያ ስራ ጀምሯል፡፡