ኢትዮጵያ ለሱዳን የሰብዓዊ ድጋፍ የ15 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ እንደምትሰጥ ገለጸች
ለሱዳናዊያን የሰብዓዊ ድጋፍ ማሰባሰቢያ መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል

በአዲስ አበባ በተካሄደው የሱዳን ሰብዓዊ ድጋፍ ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ 217 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ተዋጥቷል
ኢትዮጵያ ለሱዳን የሰብዓዊ ድጋፍ የ15 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ እንደምትሰጥ ገለጸች።
በሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ሰራዊት መካከል እየተካሄደ ያለው የእርስ በርስ ጦርነት እንደቀጠለ ይገኛል።
በዚህ ጦርነት ምክንያት 30 ሚሊዮን ሱዳናዊያን ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚስፈልጋቸው ተመድ አስታውቋል።
እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሱዳናዊያን ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ማሰባሰብን ዓላማው ያደረገ ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶኒ ጉቴሬዝ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሀማት፣ የኢጋድ ዋና ጸሀፊ ወርቅነህ ገበየሁ፣ የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬት ሚንስትር ዴኤታ ሼክ ሻክቡት ቢን ናህያን አል ናህያን እና ሌሎችም እንግዶች ተገኝተዋል።
የጉባኤው አዘጋጅ ከሆኑት መካከል አንዷ የሆነችው የተባበሩት አረብ ኢምሬት 200 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጋለች።
የአረብ ኢምሬት ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታ ሼክ ሻክቡት ቢን ናህያን በመድረኩ ላይ እንዳሉት በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ለከፋ የሰብዓዊ ጉዳት ተዳርገዋል ብለዋል።
ሚንስትሩ አክለውም "ከሁለት ሳምንት በኋላ የረመዳን ጾም ይገባል፣ ሱዳናዊያን ሰላም ይፈልጋሉ፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለሱዳን የሰብዓዊ መብት ድጋፍ እንዲያዱርግ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
እንደ ሼክ ሻክቡት ቢን ናህያን ገለጻ የተባበሩት አረብ ኢምሬት በ2024 400 ሚሊዮን ዶላር ለሱዳን የሰብዓዊ ድጋፍ ስታደርግ አሁን ደግሞ ተጨማሪ 200 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጋለች።
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ላለፉት ስድስት ዓመታት ለሱዳን ሰላም ድጋፍ ስታደርግ ቆይታለች ብለዋል።
"ሁሉም ሱዳናዊያን ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጡ እጠይቃለሁ፣ ኢትዮጵያም እንደ ከዚህ በፊቱ ሁሉ ከሱዳናዊያን ጎን ትቆማለች" ሲሉም በንግግራቸው ላይ ጠቅሰዋል።
እንዲሁም ኢትዮጵያ ለሱዳን የ15 ሚሊዮን ዶላር የሰብዓዊ ድጋፍ እንደምታደርግም ተናግረዋል።
የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ለሱዳን አንድ ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግም በመድረኩ ላይ አሳውቀዋል።
ጅቡቲ፣ ሞሮኮ እና ሌሎችም ሀገራት በድምሩ 217 ሚሊዮን ዶላር ለሱዳን የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።
ብሪታንያ፣ አሜሪካ፣ ስዊድን፣ ጣልያን፣ ሆላንድ እና ሌሎችም የዓለማችን ሀገራት ለሱዳን የሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆናቸው ተናግረዋል በተመድ የሰብዓዊ ድጋፍ ድርጅቶች እና በተናጥል ድጋፍ ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ በተወካዮቻቸው በኩል ተናግረዋል።