በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊን አሁናዊ ሁኔታ ምን ይመስላል?
ኢትዮጵያዊያን በሐሰተኛ መረጃዎች እየተታለሉ አሁንም በጦርነት እና በኢኮኖሚ ቀውስ ወደ ምትታመሰው ሊባኖስ እየመጡ ነው ተብሏል
ጦርነቱን ተከትሎ በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት አሰሪዎች የተጠራቀመባቸውን ደመወዝ ላለመክፈል በመጠለያ ጣቢያዎች ጥለዋቸው የሄዱ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉ ሰምተናል
በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊን አሁናዊ ሁኔታ ምን ይመስላል?
እስራኤል እና የሊባኖሱ ሂዝቦላህ የተኩስ አቁም መፈራረማቸውን ተከትሎ አንድ ዓመት ያለፈው የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት አሁን ላይ ቆሟል፡፡
ኢትዮጵያዊያን ከሚኖሩባቸው የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ሊባኖስ ዋና ከተማዋ ቤሩትን ጨምሮ ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች በእስራኤል የአየር ላይ ጥቃት ሲደበደቡ ቆይተዋል፡፡
ይህ ጦርነት በሊባኖስ የሚኖሩ ከ30 ሸህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ከቀሪው የሀገሪቱ ዜጎች ጋር የደህንት ስጋት ውስጥ ወድቀው ቆይተው ነበር፡፡
ጦርነቱ መቆሙን ተከትሎ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀድሞ ቤታቸው በመመለስ ላይ ሲሆኑ ኢትዮጵያዊያኑ በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ አል-ዐይን አማርኛ በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ጠይቋል፡፡
በሀገሪቱ ዋና ከተማ ቤሩት ከአሰሪዎቿ ጋር እንደምትኖር እና ስሟ ለደህንነቷ በመስጋት እንዳይጠቀስ የፈለገች አንድ ኢትዮጵያዊት እንዳለችው “አሁን ያለው ድባብ በጣም ደስ ይላል፣ የመሳሪያ ድምጽ እየተሰማ አይደለም፡፡ ተፈናቅለው የነበሩ እና መጠለያ ውስጥ ሲኖሩ የነበሩ ሰዎች ወደ ቤታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ ከባድ ጊዜ ነው ያሳለፍነው፣ ያሳለፍነውን ስቃይ እንዴት እንደምረሳው አላውቅም” ብላለች፡፡
በጦርነቱ የቆሰሉ ወይም የሞቱ ኢትዮጵያዊን ይኖሩ ይሆን? ብለን ላነሳንላት ጥያቄም “እስካሁን በጦርነቱ ምክንያት የቆሰለ እና የሞተ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ስለመኖሩ አልሰማሁም” ስትል ተናግራለች፡፡
በጦርነቱ ውስጥ ሆነን ከኢትዮጵያ የሚመጡ ኢትዮጵያዊያን አሉ፣ ደላሎች አሁንም በጉብኝት ቪዛ ምንም አይነት ስለሀገሩ መረጃ የሌላቸውን ዜጎች ወደ ሊባኖስ ሲያስገቡ እንደነበር የተናገረችው አስተያየት ሰጪዋ ወጣት እህቶቻችን በመረጃ እጥረት ምክንያት እየተጎዱ መሆኑንም አክላለች፡፡
ጦርነቱ ቆመ እንጂ አሁንም የኑሮ ውድነቱ እና ረሃብ አለ የምትለው ይህች ኢትዮጵያዊት በሀገሪቱ በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት ኢትዮጵያዊያን ለዓመታት የሰሩበት ደመወዝ እስካሁን እንዳልተከፈላቸው ነግራናለች፡፡
በተለይም በጦርነቱ የተፈናቀሉ አሰሪዎች ጦርነቱ ቆሞ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ የተጠራቀመባቸውን ደመወዝ ላለመክፈል ኢትዮጵያዊኑን ሜዳ ላይ ጥለዋቸው የሄዱ አሰሪዎች አሉም ተብሏል፡፡
በየቀኑ ሚሳኤል በሚተኮስባት ዩክሬን ኢትዮጵያዊያን እንዴት እየኖሩ ነው?
ሌላኛዋ ጆኒ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ስትኖር እንደነበር እና አሁን ወደ ቤሩት መምጣቷን የነገረችን አስተያየት ሰጪ ደመወዛቸውን፣ፓስፖርታቸው እና ሌሎች የጉዞ ሰነዶቻቸውን በአሰሪዎቻቸው የተነጠቁ ኢትዮጵያዊያን ብዙ መሆናቸውን ተናግራለች፡፡
አስተያየት ሰጪዋ አክላም “በሊባኖስ የትኛውም ቦታ ላይ እርዳታ የሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያንን ማየት የተለመደ ነው” ያለች ሲሆን በጦርነቱ ወቅት መጠለያዎች ተዘጋጅተው ስለነበር እኛም እንደማንኛውም ዜጋ አልተቸገርንም ነበር፣ አሁን ሰዎች ወደ ቤታቸው ሲሄዱ የሚረዳን ልናጣ እንችላለን የሚል ስጋት እንዳላት ገልጻለች፡፡
ሊባኖስ ወደ ቀድሞ ሰላም እና ኢኮኖሚዋ እስከምትመለስ ድረስ ኢትዮጵያዊያን እንዳይመጡ እመክራለሁ የምትለው አስተያየት ሰጪዋ በተለይም የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ይህን እንዲያስቆሙም አሳስባለች፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሊባኖስ ባሉ ኢትዮጵያዊያን ላይ ከዚህ በፊት በነበሩ እና አዲስ በተከሰቱ ችግሮች ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጠን ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡
ሚኒስቴሩ ከአንድ ወር በፊት በሁለት ዙሮች በሊባኖስ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 125 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ አድርጌያለሁ ማለቱ ይታወሳል፡፡