ኢትዮጵያ በሃይልና በወረራ ማሳካት የምትፈልገው ነገር የለም - ጠ/ሚ ዐቢይ
የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊትም “በሃይል ፍላጎቶቻችን ለማሳካት ቃታ እንደማይስብ አረጋግጥላችኋለሁ” ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ
116ኛ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ቀን በአዲስ አበባ ተከብሯል
ኢትዮጵያ በሃይል እና በወረራ ማሳካት የምትፈልገው ነገር የለም አሉ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ እና የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ 116ኛው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ቀን በአዲስ አበባ ሲከበር ባደረጉት ንግግር፥ የመከላከያ ሠራዊት ዋነኛ ዓላማው ሰላምን ማጽናት መሆኑን አንስተዋል።
የመከላከያ ሰራዊት በሃይል የሀገሪቱን ፍላጎት ለማሳካት ቃታ እንደማይስብም ነው የተናገሩት።
- ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን ለመጠቀም እንደምትደራደር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናገሩ
- ስለባህር በር የሚደረጉ ንግግሮች ግራ አጋቢ እንደሆኑበት የኤርትራ መንግስት ገለጸ
“በውጊያ ከማሸነፍ በሰላም ማሸነፍ እጅጉን ይበልጣል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ መላው የኢትዮጵያ ሃይል በድርድር በውይይት ኢትዮጵያን የሚያጸና ስራን እንዲያከናውን ጥሪ አቅርበዋል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከኢትዮጵያ ያነሰ ዓላማ የለውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ “ሰራዊቱ የተደራጀው ለኢትዮጵያውያን፣ የሚመራው በኢትዮጵያውያን እና የሚሰራው ለኢትዮጵያ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በበኩላቸው ሉዓላዊነቷ ሳይደፈር የተረከብናትን ሀገር እንደታፈረችና እንደተከበረች ለማስቀጠል ዝግጁ መሆናችንን ለሕዝባችን እናረጋግጣለንም ብለዋል።
“የሠራዊታችንን ዝግጁነት በማዳበር የማድረግ ዐቅማችንን በማሣደግ የውጭም ሆነ የውስጥ የጸጥታ ሥጋትን እየመከትን ነው” ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የምድር፣ የዓየር፣ የባህር እና የሳይበር ኃይላችን ዘመኑን እና ኢትዮጵያን በሚመጥን ሁኔታ በመገንባት አስተማማኝ ደረጃ ላይ አድርሰናል ነው ያሉት፡፡
በሱዳን የተከሰተው ችግር በኢትዮጵያም እንዳይከሰት በማሰብ የታጠቁ ኃይሎችን እና ኢ- መደበኛ አደረጃጀቶችን ወደ ህጋዊ መስመር ለማስገባት እየተሠራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ኢትዮጵያ በዘመናዊ መልኩ የመከላከያ ሰራዊት ያደራጀችው ጥቅምት 15 ቀን 1900 ዓ.ም እንደነበር ይነገራል።
የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ አጼ ምኒሊክም ፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ (አባ መላ)ን የመጀመሪያው የጦር ሚኒስትር አድርገው መሾማቸው የሚታወስ ነው።