ጠ/ሚ ዐቢይ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ለትግራይ ህዝብ ያላያቸውን የተግባር ወንድምነትና አጋርነት ለማሳየት ወደ መቀሌ እንደሚሄዱ ይሄዳሉ ብለው ነበር
የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ልዑካን ቡድን ዛሬ ማለዳ መቀሌ ገብቷል።
በብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፈራህ የተመራው ልዑኩ የሁሉም ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች እና የብልፅግና ፓርቲ አመራሮችን ያካተተ ነው መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።
ልዑካን ቡድኑ መቀሌ አሉላ አባነጋ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች አቀባበል አድርገውለታል።
የጉዞው ዓላማም ያነቡ ዓይኖችን እንባ ለማበስና የወደሙ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ክልሎች እንደወንድም ህዝብ ካላቸው ለማጋራት እና የሰላም ጅማሮውን በተግባር ለማስቀጠል ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባሳለፍነው ዕሁድ "ጦርነት ይብቃ-ሰላምን እናፅና" በሚል መሪ ቃል በተካሄደው የሰላም የዕውቅና መርሐ-ግብር ላይ የሁሉም ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ለትግራይ ህዝብ ያላያቸውን የተግባር ወንድምነትና አጋርነት ለማሳየት ወደ መቀሌ እንደሚሄዱ ገልጸው ነበር።
መንግሥት እና ህወሓት ለሁለት ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ጦርነት ለማቆም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም የሰላም ስምምነት መፈራረማቸው ይታወቃል።