የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳድር 27 አባላት ያሉት ካቢኔ አቋቋመ
የክልሉ የቀድሞ መሪ የነበሩት ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ የስልጣን ርክክብ አድርገዋል
የቀድሞ ሀገር መከላከያ አዛዦች ጀነራል ታደሰ ወረደ እና ጀነራል ፃድቃን ገብረተንሳይ በምክትል ፕሬዝዳንትነት ተሹመዋል
የህወሀት ቃል አቀባይ በሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር 27 አባላት ያሉት የካቢኔ አባላት ይፋ ማድረጋቸውን ትግራይ ቴሌቪዥን ዘግቧል።
በክልሉ መዲና መቀሌ ከተማ የተካሄደ ይህ የመንግስት ምስረታ ትግራይ ክልል ከሁለት ዓመት በኋላ ህጋዊ እና አካታች መንግሥት መመስረቱ ተገልጿል።
አዲሱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ መንግሥትን አቶ ጌታቸው ረዳ ፕሬዝዳንት፣ የቀድሞ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራር የነበሩት ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ እና ጀነራል ጻቅድቃን ገብረትንሳኤ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ተሹመዋል።
ጀነራል ታደሰ የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት እንዲሁም የሰላም እና ጸጥታ ካቢኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊ ሆነው ሲሾሙ ሌተናል ጄነራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ ደግሞ በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ ያልተማከለ አስተዳደር እና ዴሞክራታይዜሽን ካቢኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል።
በሹመቱ ይፋዊ ስነ ስርዓት ወቅትም የቀድሞው የክልሉ አመራሮች ስልጣኑን በጊዜያዊ አስተዳደሩ ለተቋቋመው አዲሱ ካቢኔ አስረክቧል።
አዲሱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ካቢኔ የተዋቀረው ከህወሓት፣ ከትግራይ ኃይሎች፣ ከምሁራን እና ከብሔራዊ ባይቶ አባይ ትግራይ (ባይቶና) ፖለቲካ ፓርቲ የተውጣጡ አባላትን ያካተተ ነው ተብሏል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሽብርተኝነት ዝርዝር ውስጥ ከሁለት ሳምንት በፊት የተሰረዘው ህወሀት የጊዜያዊ አስተዳድር ካቢኔ ሹመቶች ውስጥ 51 በመቶውን ቦታ ሲይዝ ተቃዋሚው ባይቶና ፓርቲ ሁለት ቢሮዎችን በኃላፊነት የመምራት ዕድል አግኝቷል ተብሏል።
ከትግራይ ታጣቂ ኃይሎች ውስጥ ደግሞ ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ፣ ብርጋዴር ጄነራል ተኽላይ አሸብር፣ ሌተናን ጄነራል ፍሰሃ ኪዳኑ እና ሜጀር ጄነራል ዘውዱ ኪሮስ ናቸው።
ከስድስት ወር በፊት የፌደራል መንግሥት እና ህወሀት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ የሰላም ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት ሲቆም ዛሬ የተቋቋመው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳድርም ስምምነቱ ውጤቶች መካከል አንዱ ሆኗል።