ላቭሮቭ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከመንግስት ባለስልጣናትና ከአፍሪከ ህብረት አመራሮች ጋር ይመክራሉ
የሩስያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ ገቡ።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ሚኒስትሩ አዲስ አበባ ሲገቡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
በአራት የአፍሪካ ሀገራት ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት ሰርጌ ላቭሮቭ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ዙሪያ ከመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሰርጌ ላቭሮቭ እንደፈረንጆቹ 2018 በአዲስ አበባ በኢትዮጵያ ጉብኝት አድረግው የነበረ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ እና ሩስያን ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግሩ ስምምነቶች አድርገው መመለሳቸው ይታወሳል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንም በተመሳሳይ እንደፈረንጆቹ በ2021 በሩስያ ባደረጉት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚያስችሉ የትብብር መስኮች ዙሪያ መምከራቸው የሚታወስ ነው፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ቀደም ብለው በግብጽ፣ ኮንጎ ሪፐብሊክ እና ኡጋንዳ ጉብኝት አድርገዋል፡፡