እንዲራዘሙ ከተወሰኑት ከምርጫና ከሕዝብና ቤቶች ቆጠራ የትኛው መቅደም አለበት?
ለ 3ኛ ጊዜ የተራዘመው 4ኛው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሕዝብና ቤቶቸ ቆጠራ የተካሄደው በ1976 ዓ.ም መሆኑን የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይሁንና ቆጠራ በይፋ ከመጀመሩ አስቀድሞ የሀገሪቱ ሕዝብ ቁጥር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይገመት እንደነበር ይገለጻል፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ እስካሁን የሕዝብና ቤቶቸ ቆጠራ ለሦስት ጊዜያት ተካሂዷል፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ ቆጠራ የተካሄደው በ1999 ዓ.ም ነበር፡፡ ቆጠራው በሀገሪቱ በአብዛኛው ቦታዎች በ1999 ይካሄድ እንጅ በአፋር እና ሱማሌ ክልሎች በ2000 ዓ.ም ጥቅምትና ሕዳር ወራት ነበር የተካሄደው፡፡ በወቅቱ በተደረገው ቆጠራ የሀገሪቱ የሕዝብ ቁጥር 73 ሚሊዮን 750 ሺ 932 እንደነበር ውጤቱ ያመለክታል፡፡
3ኛው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ በ1997 ዓ.ም መካሄድ ቢኖርበትም በወቅቱ ምርጫ ይደረግ ስለነበር ሁለቱን አበይት ክንውኖች ማካሄድ አስቸጋሪ በመሆኑ እንዲራዘም መወሰኑ ይታወሳል፡፡ ቆጠራው ለሁለት ዓመታት ሲራዘም ሕገ መንግስታዊ ትርጉም ተጠይቆ ነበር፡፡ ከዚያም ለ1999 ዓ.ም የተዘዋወረ ሲሆን በወቅቱ በተደረገው ቆጠራ ላይ በርካታ ቅሬታዎች ተነስተዋል፡፡ ለአብነትም የአማራና ጉራጌ ብሔሮች ከቁጥር ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ጥያቄ ሲያነሱ እንደነበር ይታወሳል፡፡
የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ በየ 10 ዓመቱ ይካሄዳል ቢባልም እንደ 3ኛው ቆጠራ ሁሉ በ2009 ይካሄድ የነበረው ቆጠራም ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡ በሀገሪቱ በነበሩ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት ሳይካሄድ የቆየው አራተኛው ዙር የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለሦስተና ጊዜ ተራዝሟል፡፡
መጋቢት 29 2011 ዓ/ም ቆጠራው ሊካሄድ እንደሚችል በማሰብ ሙያተኞችን ከማሰልጠን ጀምሮ የቆጠራ ካርታዎችን እስከማዘጋጀት የደረሱ ዝግጅቶች ሲደረጉ ነበር፡፡
ሆኖም አጋጥመው በነበሩ ሃገራዊ የሰላምና ደህንነት ችግሮች ሳቢያ ሁለቱ ምክር ቤቶች ሰኔ 3 ቀን 2011 ዓ/ም ባደረጉት ልዩ የጋራ ስብሰባ ለአንድ አመት አራዝመውታል፡፡
ከምርጫና የሕዝብ ቆጠራ የቱ መቅደም አለበት?
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሕዝብ ተመራማሪው ሲሳይ ምስጋነዉ ታምሩ (ዶ/ር) የሕዝብና ቤቶች ቆጠራን ማካሄድ የግድ የሚል ጉዳይ እንደሆነ ያነሳሉ፡፡ ይሁንና ይህንን ትልቅ ሀገራዊ ጉዳይ ለማከናወን የሀገር ሰላምና መረጋጋት በእጅጉ እንደሚያስፈልግና ሀገር ሲረጋጋ ቅድሚያ ተሰጥቶት መከናወን አለበት ብለዋል፡፡
ሲሳይ ምስጋነዉ ታምሩ (ዶ/ር)
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት 6ኛው ሀገራዊ ምርጫም እንዲራዘም መወሰኑ ይታወቃል፡፡
ከሰሞኑ የምርጫና የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ መራዘምን በተመለከተ የትኛው መቅደም አለበት በሚል ላነሳንላቸው ጥያቄ ዶ/ር ሲሳይ “ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ከምርጫው በፊት ቀድሞ መካሄድ አለበት” ብለዋል፡፡
የሕግ ባለሙያው አቶ ውብሸት ሙላት የሕዝብ ቆጠራ ውጤት ዓመታዊ የፌደራል የበጀት ድጎማ ላይ ከፍተኛ አንድምታ እንዳለው ገልጸው የበጀት ድጎማ ሲደረግ አንዱ መሥፈርት የሕዝብ ቁጥር መሆኑን አንስተዋል፡፡
በ1987 የበጀት ዓመት ለድጎማ መለኪያ የነበሩት በመቶኛ ሲገለጹ ለክልሎች ሕዝብ ብዛት 30 ከመቶ ፣ ከማዕከል ለሚኖር እርቀት 25 ከመቶ ፣ ገቢ ለማመንጨት አቅም 20 ከመቶ ፣ ከዓመት በፊት ለልማት ለተመደበው የበጀት ዓመት 15 ከመቶ ፣ እና ለክልሉ የቆዳ ስፋት 10 ከመቶ ነጥቦች ተሰጥተው እንደነበር በአብነት አንስተዋል፡፡
ይሁንና በ1988 የበጀት ዓመት ከላይ የነበሩት መነሻዎች ፡ የሕዝብ ብዛት፣ ክልሉ ያለበት የዕድገት ደረጃና በ1987 የበጀት ዓመት የሰበሰቡት የገቢ መጠን መወሰዳቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በቀጣይ ዓመትም መሥፈርቶቹ ለሕዝብ ብዛት 60 ከመቶ ፣ በልማት ላሉበት ደረጃ 25 ከመቶ እንዲሁም ላላቸው ገቢ የማመንጭት አቅም 15 ከመቶ ነጥብ መሰጠቱን የገለጹት አቶ ውብሸት የሕዝብ ብዛት ለበጀት ድጎማ ጉልህ ድርሻ ያለው መሆኑ ታውቆ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ የሚካሄድ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
አቶ ውብሸት ሙላት
ዶ/ር ሲሳይ በበኩላቸው አሁን ላይ ያለው ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የዓለም ሕዝብ ስጋት መሆኑ ሲቀርና የሰዎች እንቅስቃሴ ሲፈቀድ ከምርጫ በፊት ቆጠራ መካሄድ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ ይህም ለምርጫና ለበጀት እንዲሁም ለመሰረተ ልማት ዕቅዶች አስተዋጽኦው የጎላ እንደሚሆንም ነው ያነሱት፡፡
በኢትዮጵያ የሕዝብና ቤት ቆጠራ በየ 10 ዓመት እንደሚካሄድ፣ በውጤቱም መሰረት የምርጫ ክልሎችን አከላለል የምርጫ ቦርድ በሚያቀርበው ረቂቅ መሠረት የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት እንደሚወስን ይገልጻል፡፡
የሕዝብ ቆጠራ ማድረግ ሀገራዊ ዕቅዶችን ለማውጣት፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስትራቴጅዎችን ለመንደፍ፣ በክልሎች መካከል ፍትሃዊና የተመጣጠነ እድገትና ልማት ለማረጋገጥ ፣ የክልሎችን ፍላጎትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ ፣ ፍላጎትን መሰረት ያደረገ እቅድ ለማቀድ እና በክልሎችና በሀገር ደረጃ ሰፈራንና ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ፣እንዲሁም ለሌሎችም ጉዳዮች እንደሚጠቅም የሥነ ሕዝብ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡
በቆጠራ ወቅት መደረግ ያለበት ጥንቃቄ
እስከዛሬ የነበሩት የሕዝብና ቤቶች ቆጠራዎች ከፍተኛ የሕዝብ አመኔታ እንዳጡ የሚገልጹት ተመራማሪው በቀጣይ የሚደረገውን ቆጠራ ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ ማከናወን ይገባል ብለዋል፡፡ ከነዚህ መካከልም በሀገር ውስጥ ሰላም መፍጠር፣ ከቡድን ይልቅ የሀገርን ጥቅም ማስቀደም የመሳሰሉትን ቅድሚያ መስጠት እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት፡፡
የሕዝብ ቆጠራ ውጤት ለብዙ ውሳኔዎች በግብዓትነት ስለሚውል በአግባቡ እና በጥንቃቄ እንዲሁም በገለልተኝነት መመራት እንዳለበት ያነሱት አቶ ውብሸት ሕገ መንግሥቱ ስለ ሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽኑ ገለልተኝነት የሚለው ነገር እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ ብዝሃነት ባለበት ሀገር የሕዝብ ቆጠራ ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቅ ተግባር እንደሆነም ነው ያነሱት፡፡
የሀገሪቱ ሕገ መንግስት የሕዝብን ቁጥር በየጊዜው የሚያጠናና ቆጠራ የሚያካሂድ የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን እንደሚኖር በአንቀጽ 103 ደንግጓል፡፡ የኮሚሽኑ አባላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚሾሙ የሚደነግግ ሲሆን ዋና ጸሐፊ ፣ አስፈላጊ ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ይኖሩታልም ይላል። አሁን ያሉት የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን 20 አባላት መንግሥታዊ ኃላፊነት ላይ ያሉ ናቸው፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕዳር 18 ቀን 2011 ዓ.ም ቃለ መሃላ ፈጽመው በኮሚሽኑ አባልነት የተካተቱት ሚኒስትሮች እና የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ናቸው፡፡ ም/ል ጠ/ሚ/ር አቶ ደመቀ መኮንን የአባላቱ ሰብሳቢ ናቸው፡፡
እንደሌሎች ሀገራት ከሕዝብ ቆጠራ ጋር የሚያያዙ አለመግባባቶች እንዴት መፈታት እንዳለባቸው ግልጽ አሠራር ካለመኖሩ አኳያ ከፍተኛ ጥንቃቄን እንደሚጠይቅ የሕግ ባለሙያው ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ ከ1985 እስከ 1997 ዓ.ም ድረስ በአንጻራነት በተሻለ ሁኔታ እየተዋቀረ ሄዶ እንደአዲስ ሲዋቀር በ 1999ኙ ቆጠራ ግን ከፍተኛ ስህተት መስራቱን ይናገራሉ፡፡ ሁለቱም ባለሙያዎች ቀድሞ ከተከናወኑት የሕዝብና ቤቶች ቆጠራዎች የተሻለ ጥራት እንዲኖረው ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ተብሏል፡፡