በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚካሄደው የሶስትዮሽ ድርድር ትናንት ለሶስተኛ ቀን ተካሂዷል
ሶስቱ ሀገራት በታዛቢዎቹ ሚና ላይ መግባባታቸው ተገለጸ
በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በኢትዮጵያ ፣ ሱዳን እና ግብፅ መካከል የሚካሄደው የሶስትዮሽ ድርድር ትናንት ለሶስተኛ ቀን ተካሂዷል፡፡
ድርድሩን በማስመልከት የውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ትናንት በነበረው በቪዲዮ የታገዘ ስብሰባ ሀገራቱ በታዛቢዎች ሚና ላይ መስማማታቸውን አስታውቋል፡፡
በድርድሩ በታዛቢነት የሚሳተፉት ደቡብ አፍሪካ ፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት መሆናቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህ ታዛቢዎች በድርድሩ ላይ ከታዛቢነት ያለፈ ሚና እንዳይኖራቸው በሚል በኢትዮጵያ የተያዘው አቋም ተቀባይነት ማግኘቱን አል አይን አማርኛ ከሚኒስቴሩ ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው የሁለት ቀናት ድርድሮች ሀገራቱ በታዛቢዎች ሚና ላይ መስማማት ሳይችሉ የቆዩ ሲሆን ለዚህም እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው ግብጽ ታዛቢዎች በድርድሩ ከትዝብት ያለፈ ሚና እንዲኖራቸው መፈለጓ እንደሆነ ይገለጻል፡፡
ይሁንና ትናንት ሐሙስ ዕለት በኢትዮጵያ ሊቀመንበርነት በተካሔደው ድርድር የታዛቢዎች ሚና ላይ መግባባት እንደተደረሰ ነው የሚኒስቴሩ መግለጫ የሚያሳየው፡፡
በትናንትናው ድርድር አገራቱ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ የዉሃ ሙሌት እና አመታዊ አተገባበር ላይ በሚነሱ ስጋቶች ዙሪያ በትኩረት ተወያይተዋል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከሁለቱ የታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ጋር ውኃውን ስለምትጠቀምበት መመሪያ እንዲሁም ሱዳን ባቀረበችው ምክረ ሐሳብ ላይ ሀሳብ መለዋወጣቸው ታውቋል።
በድርድሩ ኢትዮጵያ በሦስቱ ሀገራት መካከል የሚካሔደው የውይይት ሒደት በመልካም አቀራረብ እና ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ እንዲከናወን ያላትን ጽኑ አቋም ማስታወቋም ተገልጿል።
በሶስቱ ሀገራት መካከል በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚካሔደው ውይይት ነገ ሰኔ 06 ቀን 2012 ዓ.ም በሱዳን ሊቀመንበርነት ይቀጥላል ተብሏል፡፡
ከዚህ ቀደም በግድቡ ዙሪያ ሲካሔድ የነበረው የሶስትዮሽ ድርድር ባለፈው የካቲት ወር መቋረጡ ይታወቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ አሜሪካ በታዛቢነት ገብታ አደራዳሪ ኋላ ላይም የስምምነት ሰነድ አዘጋጅ ሆናለች በሚል ፣ በዋሽንግተን በተዘጋጀው የመጨረሻ ድርድር ላይ ኢትዮጵያ ባለመሳተፏ ነው፡፡
ግብፅ ግድቡ ከአባይ ወንዝ የማገኘውን የዉሃ መጠን ይቀንስብኛል፤ ይሔም ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ቀውስ ያስከትልብኛል የሚል እምነት ሲኖራት ኢትዮጵያ ደግሞ ግብፅና ሱዳን ላይ ጉልህ ጉዳት በማያደርስ መልኩ የተፈጥሮ ሀብቴን እጠቀማለሁ የሚል ጽኑ አቋም ይዛለች፡፡
ከግድቡ ጋር በተያያዘ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ፖለቲካዊ ዉጥረት እየተካረረ ባለበት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ እና ሱዳን ድርድሩ እንዲቀጥል በጠቅላይ ሚኒስትሮቻቸው ዉይይት መስማማታቸውን ተከትሎ ነው ድርድሩ በድጋሚ መካሔድ የጀመረው፡፡