ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ መራዘሙ እና የትግራይ ክልል የተለየ አቋም የወቅቱ መነጋገሪያ ሆነዋል
ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ መራዘሙ እና የትግራይ ክልል የተለየ አቋም የወቅቱ መነጋገሪያ ሆነዋል
በኢትዮጵያ በነሐሴ 2012 ዓ/ም ሊደረግ ታስቦ የነበረው ሀገር አቀፍ ምርጫ በወቅታዊው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የቅድመ ምርጫ ተግባራት በተያዘላቸው ጊዜ ሊካሄዱ አለመቻላቸውን ተከትሎ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ሊከናወን እንደማይችል አሳውቋል፡፡ ነገር ግን ሀገራዊ ምርጫው መቼ ሊካሄድ እንደሚችል የተባለ ነገር የለም፡፡ ይሄ ጉዳይ የወቅቱ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል፡፡
የትግራይ ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሓት) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ ብልፅግና ፓርቲ ቀድሞውኑም የ2012 ሀገር አቀፍ ምርጫን ለማከናወን ሙሉ ፈቃደኝነት አላሳየም ሲል ወንጅሏል፡፡
“ብልፅግና ፓርቲ የኮሮና ቫረስ ወረርሽኝ መከሰትን እንደመልካም አጋጣሚ በመቁጠር በአንድ ሰው የሚመራ አምባገነን ሥርዓትን ለመትከልና ከሕገ-መንግስታዊ መንገድ ውጪ የሥልጣን ዕድሜን ለማራዘም እየሰራ ነው” ሲል በመግለጫው አካቷል፡፡
“የብልፅግና ፓርቲ ሕገ-መንግስቱን ለመተርጐም በሚል ሰበብ የጀመረውን ገሀድ የወጣ እንቅስቃሴ በአስቸኳይ ማቆም አለበት፤ ሕገ-መንግስታዊ ትርጓሜ የሚያስፈልገው ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓት ባስቀመጠው ግልፅ መስፈርት መሰረት አሻሚ ሁኖ ለተገኙ አንቀፆች ነው” ሲል ህወሓት አቋሙን አስቀምጧል፡፡
ፓርቲው ክልላዊ ምርጫ ለማድረግ ዝግጅት እንዲደረግ መወሰኑንም ባወጣው መግለጫ ላይ አስፍሯል፡፡
የህግ አማካሪና ጠበቃ ሞላልኝ መለሰ፣ አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት ሁኔታ ምርጫውን በተጣበበ ሁኔታ ማድረግ እንደማይቻል ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስለገለጸ ምርጫውን ማድረግን በአማራጭነት ማቅረብ እንደማይቻል አስታውቀዋል፡፡ በዚህም መሰረት ህወሓት ምርጫው በተያዘለት ጊዜ ሰሌዳ እንዲካሄድ ያቀረበው ሃሳብ ሀገራችን ያለችበትን ወቅታዊ የኮሮና በሽታ ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ ስለሆነ ተቀባይነት እንደሌለው ነው ባለሙያው የሚያነሱት፡፡
የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 102 “በፌዴራልና በክልል የምርጫ ክልሎች ነፃና ትክክለኛ ምርጫ በገለልተኝነት እንዲያካሂድ ከማንኛውም ተፅዕኖ ነፃ የሆነ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ይቋቋማል፤ የቦርዱ አባላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማሉ፤ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል” ይላል፡፡ የህግ ባለሙያው በዚህ መሰረት ክልሎች ምርጫ እንዲያደርጉ ሥልጣን አልተሰጣቸውም ሲሉ ነው የገለጹት፡፡
ሌላው የህግ ባለሙያ አቶ አሮን ደጎልም ተመሳሳይ ሃሳብ አላቸው፡፡ ምርጫን በተመለከተ ክልሎች ህግ ማውጣት እንደማይችሉ የገለጹት አቶ አሮን ደጎል ክልሎች የንግድ ህግና የአሰሪና ሰራተኛ ህግ ማውጣት እንደማይችሉት ሁሉ የምርጫ ህግን የማውጣት ሥልጣን የላቸውም ብለዋል፡፡ ”ምርጫ የሚካሄድበትን ሥርዓት ህግ የማውጣት ስራ የፌዴራል መንግስት ስልጣን ነው፤ የምርጫ ቦርድ ደግሞ የሚቋቋመው በፌዴራል መንግስቱ ነው፤ አባላቱም የሚሾሙት በፌዴራል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፤ ስለዚህ ክልሎች ኢ-ሕገ መንግሥታዊ የሆነ እንቅስቃሴ ማድረግ አይጠበቅባቸውም” ሲሉ ነው አቶ አሮን የሚያነሱት፡፡
የህግ ባለሙያው አቶ አለማየሁ ባጫ ምርጫዎች እንዲዘጋጁ፣ ነጻና ፍትሃዊ እንዲሆኑም የማድረግ ስልጣን ያለው ምርጫ ቦርድ ብቻ መሆኑን ገልጸው፣ “አንተ በራስህ የምታደርገው ሕገ መንግሥታዊ አይሆንም፤ በአንቀጽ 93 መሰረት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት የታገዱ መብቶች አሉ” ይላሉ፡፡
አቶ ብስራት ተክሉም የህግ ባለሙያ ሲሆኑ፣ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 51 ንዑስ አንቀጽ 15፣ የፌደራሉ መንግስት “በዚህ ሕገ መንግሥት የተረጋገጡትን የፖለቲካ መብቶች ለማስፈጸም አስፈላጊ የሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶችን እንዲሁም ምርጫን በሚመለከት ሕጐች ያወጣል“ የሚለውን በመጥቀስ፣ “ይህ ድንጋጌ እንደሚለው በኢትዮጵያ የክልል መንግስታት ምርጫን ማድረግ አይችሉም ” ብለዋል፡፡
የፌደራልም ሆነ የክልል ምርጫን ማካሄድ የሚያስችል ስልጣም ያለው የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ መሆኑን የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳም ገልጸዋል፡፡
ሰብሳቢዋ ይሄን ያሉት ህዝበ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከትናንት በስቲያ፣ ሚያዝያ 26/2012 ዓ.ም፣ ባወጣው መግለጫ ክልላዊ ምርጫ ለማካሄድ ተዘጋጅቻለሁ የሚል መግላጫ ማውጣቱን ተከትሎ የቦርዱ አስተያየት ምን እንደሆነ ኢቢሲ ላነሳላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ ነው፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ፣ ምርጫው እንዲራዘም መግባባት ላይ ደርሶ ለዚህም የሕገ መንግሥት ትርጓሜ እንዲሰጥ ዉሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል፡፡