ኢዜማ የምክር ቤቱን የስልጣን ዘመን የሚገድበው የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 58/3 እንዲሻሻል በአማራጭነት ጠይቋል
ኢዜማ የምክር ቤቱን የስልጣን ዘመን የሚገድበው የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 58/3 እንዲሻሻል በአማራጭነት ጠይቋል
አሁን ላይ የሚሰጠው ህጋዊና ፖለቲካዊ አማራጭ ህዝብን ከወቅታዊው የኮሮና ወረርሽኝ የሚታደግ፣ ሀገረ-መንግሥቱን የሚያስቀጥልና ወደ ተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገውን ሽግግር የሚያግዝ ሊሆን እንደሚገባ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ባወጣው መግለጫ ጠየቀ፡፡
ወረርሽኙ በኢትዮጵያ እስከካሁን ያስከተለው ጉዳት ከሌሎች ሀገሮች ጋር ሲነጻጸር አስከፊ የሚባል ባይሆንም የደቀነው አደጋ ግን ከፍተኛ እንደሆነ የገለጸው ፓርቲው በሌሎች ሀገራት ከታየው ተሞክሮ አንፃር ወረርሽኙ ድንገት በከፍተኛ ቁጥር ዜጎችን ሊያጠቃ እና የጤና ሥርዓት ቀውስ ውስጥ ሊከተን የሚችልበት አደጋ አለ ብሏል፡፡ በጎረቤት ሀገሮች (ሱዳን፣ ጅቡቲና ሶማሊያ) የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በፍጥነት መዛመት፣ በተለይ ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ጋር ካላት የቀረበ የኢኮኖሚ ትስስር አንፃር በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል ላይ የደቀነው ስጋት ከፍተኛ እንደሆነ ኢዜማ አንስቷል፡፡
”በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ የወረርሽኙ ተጽዕኖ ከኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ጫና በተጨማሪ በፖለቲካው ዘርፍም በታሪካችን አጋጥሞን የማያውቅ ሁኔታ ውስጥ ከቶናል” ሲል ኢዜማ ገልጿል፡፡
ከወረርሽኙ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም የነበሩ የውስጥ ፖለቲካዊ ችግሮች እና በዓባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ካለው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጋር በተያየዘ ሀገሪቱ ከሌሎች ሀገሮች የተደቀነባት አደጋ በፍፁም በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ እንዳልሆነና በተለይም ከግድቡ የውሃ ሙሌት ጋር ተያይዞ የሚመጣው ተጽዕኖ እየጨመረ ሊሄድ እንደሚችልም ፓርቲው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባወጣው መግለጫ ላይ አስፍሯል፡፡
ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መካሄድ አለመቻሉን ተከትሎ የተፈጠረውን ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ በተመለከተ፣ ኢዜማ ከሕግ ባለሙያዎች በተለይም ከሕገ መንግሥት ጠበቆች ጋር ሰፊ ውይይት አድርጎ፣ በወቅቱ ትልቅ ጥያቄ ላይ ጊዜ ሰጥተው እንዲመክሩበት የከፍተኛ ባለሙያዎች ጉባዔ በማቋቋም ለአንድ ወር ጉዳዩን ሲያስጠናና ምክክር ሲያስደርግበት መቆየቱንም ይፋ አድርጓል፡፡
ከተለያዩ አካላት የሚቀርቡ ሀሳቦች ሀገሪቱን ብዙ ዋጋ በማያስከፍል የተሻለ አማራጭ ላይ ትኩረት ያደረጉ መሆን እንዳለባቸውና በፍጥነት የተቀያየሩትን የኢትዮጵያንና የቀጠናውን ጂኦ ፖለቲካዊና የደህንነት ስጋቶች በሚገባ ከግምት ውስጥ ያስገቡ ሊሆኑ እንደሚገባ ኢዜማ በመግለጫው ላይ አስፍሯል፡፡
ሀገራዊ ፈተናዎችን ለማለፍ ሕዝብን አስተባብሮ ሊመራ የሚችል ጠንካራ መንግሥት ያስፈልጋል ብሏል ኢዜማ፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች ንግግር ላይ የተመሰረተ የሽግግር መንግሥት ሀገሪቱን ሊመራ ይገባል የሚል ሃሳብ ከተለያዩ አካላት እየቀረበ መሆኑን የገለጸው ኢዜማ፣ ይህ ሀሳብ አሁን ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነት እና የቁጥር ብዛት ከግምት ያላስገባ በመሆኑ ተግባራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ ስለመሆኑም ነው ያስታወቀው፡፡
ይህ የመፍትሔ hሳብ እንደ ሀገር ያሉትን ፈተናዎች ተጋፍጦ ለማለፍ የሚያስፈልገውን ጠንካራ የመንግሥት መዋቅር የሚፈጥር እንዳልሆነ የገለጸው ፓርቲው ሀገሪቱ የገባችበትን ችግር ከመፍታት ይልቅ ወደ ባሰ ሀገራዊ ቀውስ ሊከተን የሚችል አማራጭ እንደሆነም ነው የገለጸው፡፡
“በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 104 እና 105 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ማድረግ በግልጽ የተቀመጠ የማስፈጸሚያ ሥነ ሥርዓት ያለው በመሆኑ እንዲሁም አሁን ለገባንበት አጣብቂኝ የማያዳግም ምላሽ የሚሰጥ ሆኖ አግኝተነዋል” ሲል ኢዜማ የህገ መንግስት ማሻሻያ ማድረግ የተሻለ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ይሁንና ፓርቲው በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ሊሻሻሉ የሚገባቸው በርካታ አንቀጾች እንዳሉ በፅኑ ቢያምንም አሁን ላይ ወቅቱ ሁሉን አቀፍ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አለመሆኑን እና አሁን ሀገሪቱ ለገባችበት አጣብቂኝም ቀልጣፋ ምላሽ እንደማይሰጥም ጠቅሷል፡፡
የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 58 ንዑስ አንቀጽ 3 “የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ነው፤ የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሒዶ ይጠናቀቃል” ቢልም ጊዜውን ጠብቆ ምርጫ ለማድረግ የማያስችል ድንገተኛ እና ከአቅም በላይ የሆነ ችግር በሚያጋጥምበት ጊዜ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከ1 ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ምርጫውን እንዲያራዝም የሚል ሀሳብ ተጨምሮበት ሊሻሻል ይገባል ብሏል ኢዜማ፡፡ የታክስ እና የግብር ሥልጣንን የሚደነግገው አንቀጽ 98 እና የሕዝብ ቆጠራን የሚመለተው አንቀጽ 103 ከዚህ ቀደም የተሻሻሉበትን እንደመነሻ መውሰድ እንደሚቻልም ፓርቲው አስታውቋል፡፡
ኢዜማ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 58 ንዑስ አንቀጽ 3 ማሻሻል የተሻለ አማራጭ መሆኑን ቢገልጽም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 54 ንዑስ አንቀጽ 1፤ አንቀጽ 58 ንዑስ አንቀጽ 3 እና አንቀጽ 93 ላይ ትርጉም እንዲሰጥ ለፌደሬሽን ምክር ቤት መምራቱ የተሻለ አማራጭ ነው ብሎ እንደማያምን ገልጿል፡፡ ይሁንና ይህ ተግባራዊ ከተደረገ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔው ሕገ መንግሥቱን በሚተረጉምበት ወቅት ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ ማንኛውም አካል ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ ተግባሩን ማከናወን እንዳለበትም አሳስቧል፡፡
የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በሚያቀርበው የውሳኔ ሀሳብ የፌደሬሽን ምክር ቤት የሚያጸድቀው ትርጉም የመንግሥትን ሥልጣን በማንኛውም መልኩ የሚያራዘም ከሆነ ማራዘሚያውን እጅግ ቢገፋ ከ1 ዓመት እንዳይበልጥ ማድረግ እንዳለበት የገለጸው ፓርቲው ውሳኔው በዚህ የማራዘሚያ ወቅት ሥልጣን ላይ የሚቆየው መንግሥት ዘላቂ ውጤት ያላቸውን እና በቀጣይ ምርጫውን አሸንፎ ሥልጣን በሚይዘው መንግሥት ላይ ተጨማሪ ኃላፊነትን የሚጥሉ ተግባራትን ከመፈፀም እንዲቆጠብ የሚያስገድድ መሆን እንዳለበትም በመግለጫው አሳስቧል፡፡
እንደሀገር የሚወሰዱ ማናቸውም አማራጮች ሀገሪቱ አሁን ያለችበትን አስቸጋሪ እና ፈታኝ ወቅት ከግምት ያስገቡ፣ የሀገር መረጋጋት፣ ሰላም እና ቀጣይነትን የሚያረጋግጡ፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደቱን የሚያስቀጥሉ እንዲሁም አሁን ከገባንበት ሕገ መንግሥታዊ አጣብቂኝ በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስወጡን መሆን እንዳለባቸው ኢዜማ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች በተመሳሳይ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ በቂ እና ቀጣይነት ያለው ውይይት የሚያደርጉበት መድረክ እንዲመቻችም ጠይቋል።