በቻይና የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን ሁኔታ የሚከታተል ግብረ ኃይል ተቋቁሟል
በቻይና የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን ሁኔታ የሚከታተል ግብረ ኃይል ተቋቁሟል፡፡
የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአፍሪካ ህብረት ጉባኤ እና በጉባኤው የኢትዮጵያን ተሳትፎ ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው በመግለጫቸው እንዳሉት የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቁ ውሳኔዎች የተላለፉበት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለህብረቱ እና ለተባበሩት መንግስታት ሁለት፣ ሁለት የአባልነት ቦታዎች ያቀረበቻቸው አራት እጩዎች ተቀባይነት ማግኘታቸውንም ተናግረዋል፡፡
በቻይና የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን በተመለከተ ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ተማሪዎቹ የኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ እንዳይሆኑ በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሀገሪቱ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ከሚገኙ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ጋር በቅርበት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
ለመመለስ ጥያቄ ያቀረቡ ተማሪዎችም መኖራቸውን የገለጹት አቶ ነብያት ለዚህም በመንግስት የተቋቋመ ግብረ ኃይል በቅንጅት እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የተማሪዎቹን ሁኔታ ለመከታተል የተቋቋመው ግብረ ኃይል ከቻይና መንግስት ጋር የመወያየትና ሌሎችንም ስራዎች እንደጀመረ የተናገሩት አቶ ነቢያት ጌታቸው እስከሚመለሱ ድረስ ባሉበት ሆነው በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና ውሃን በሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ በኩል መንግስት የገንዘብ ድጋፍ መላኩን ጠቁመዋል፡፡
ቃል አቀባዩ እስካሁን ከተማሪዎቹ መካከል በቫይረሱ የተያዘ የለም ያሉ ሲሆን ከመንግስት የተላከው የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አቅመ ደካማ ለሆኑ ተማሪዎች ከዛሬ ጀምሮ እንደሚደርሳቸው ተናግረዋል፡፡
ቫይረሱ በተከሰተበት በውሃን ከተማ ብቻ ከ300 በላይ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ይገኛሉ፡፡
ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ የሚካሔደው የሶስትዮሽ ውይይት ጉዳይ ሌላው በመግለጫው ወቅት የተነሳ ጥያቄ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅን በተመለከተ ከየካቲት 4-5 ቀን 2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን መካከል ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ለማዘጀት የተካሔደው ውይይት ያለስምምነት መጠናቀቁ ይታወቃል፡፡
ኢትዮጵያ ጥቅሟን የሚጎዳ ስምምነት በምንም መንገድ አትፈጽምም ያሉት ቃል አቀባዩ ድርድሩ ያለስምምነት የተቋጨውም ከዚሁ ጋር በተያያዘ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ጋር በተያያዘ በተሰራ ስራ ደግሞ 128 ኢትዮጵያውያን ዛሬ ከታንዛኒያ ይመለሳሉ ብለዋል፡፡ ተመላሾቹ በተለያዩ የታንዛኒያ እስር ቤቶች የነበሩ ናቸው፡፡ ከአሁን ቀደምም በመካከለኛው ምስራቅ እና በሌሎችም የአፍሪካ ሃገራት በእስር ላይ የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገራቸው መመለሳቸው የሚታወስ ነው፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ በመጪው ሰኞ ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙም አቶ ነቢያት ጌታቸው ተናግረዋል፡፡
የፖምፒዮ ጉብኝት በጸጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ያተኩራል ያሉት አቶ ነቢያት ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ አቻቸው አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ እንዲሁም ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሀማት ጋር እንደሚመክሩ ገልጸዋል፡፡