በትግራይ ክልል ከሚገኙ ተማሪዎች ሰባት በመቶው በጥይት ተመተው ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገለፀ
የሰሜኑ ጦርነት በትግራይ ተማሪዎች ላይ ያደረሰውን ተጽዕኖና የትምህርት ኪሳራ የሚሳይ ጥናት ይፋ ሆነ
በሰሜኑ ጦርነት የትግራይ ተማሪዎች ላይ የደረው ቁስል ‘አስደንጋጭ’ መሆኑ ተመላክቷል
ከሁለት ዓመታት በላይ የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ዳፋ ህጻናት ላይ ግዙፍ መሆኑ ተነግሯል፤በተለይም ጦርነቱ በትግራይ ተማሪዎች ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ የዓመታትን የቤት ስራ የሚጠይቅ ነው ተብሏል።
በጦርነቱ ሳቢያ በትግራይ ክልል 75 በመቶ ከ2ተኛ እስከ 4ተኛ ክፍል ተማሪዎች ቃላት ማንበብ ጨምሮ የተማሩትን መርሳታቸው በጥናት ተረጋግጧል።
ይህም ከፍተኛ የትምትህርትን ኪሳራን የሚያሳይ ነው ያሉት አጥኝዎች፤ ተማሪዎቹን በማንበብ፣ ፊደል በመለየት፣ አንብቦ በመረዳት እንዲሁም በእንግሊዘኛና በሂሳብ የትምህርት ዘርፎች መዝነዋቸዋል።
በሰሜኑ ጦርነት በትግራይ ህጻናት ላይ የደረውን የትምህርትና የስነ-ልቦና ጫና የሚየሳይ ጥናት ሉምኖስ ፈንድ በተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ይፋ ተደርጓል።
በተማሪዎች፣ መምህራንና ወላጆች ላይ የተደረገው ጥናት አሳሳቢ የተባለ ውጤት ማሳየቱን የድርጅቱ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አለማየሁ ኃይሉ (ዶ/ር) ለአል ዐይን ተናግረዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና አላቸው በተባሉ የአዕምሮ ቁስል (ትራማ) መለኪያዎች የተገኘውን ውጤት “አስደንጋጭ” ነው ብለዋል። ጥናቱ በናሙና ከወሰዳቸው ተማሪዎች መሀል ሰባት በመቶ ተማሪዎች (ህጻናት) በጥይት ተመተዋል። ዘጠኝ በመቶ መምህራንና 11 በመቶ ወላጆችም በጥይት መመታታቸውን ሉምኖስ ፈንድ ገልጿል።
40 በመቶ ህጻናቱ ሴቶች ሲደፈሩ ማየታቸውን ያረጋገጠው ጥናቱ፤ "ጅምላ ግድያን ጨምሮ ሰው ሲገደል ያዩ፣ ሰዎች በመሳሪያ ያስፈራራቸው፣ የቆሰለ ሰውና አስከሬን እንዲሸከሙ የተገደዱ፣ ቤታቸው ላይ ከባድ መሳሪያ የወደቀባቸውና ከቤታቸው እንዲወጡ የተገደዱ" በርካታ ናቸው ተብሏል።
በትግራይ የኮቪድ ወረርሽኝን ጨምሮ በጦርነቱ ለአራት ዓመታት ትምህርት እንዳልነበር ክልሉ አስታውቋል። የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ኪሮስ ገዑሽ (ዶ/ር) ከዚህ ባሻገር በጦርነቱ የትምህርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ማድረሱን ገልጸዋል።
የትምህርት መሰረተ-ልማት፣ የሰው ኃይል (የመምህራን ህልፈት) እንዲሁም በስርዓተ-ትምህርቱ ዘርፉ ውድቀት እንደገጠመው ኃላፊው ለአል ዐይን ተናግረዋል። ከጦርነቱ በፊት “ደህና” ሊባል የሚችል የትምህርት አኳኋን ላይ ነበርን የሚሉት ኃላፊው ወድመቱ ግዙፍ መሆኑን ገልጸዋል።
አራት ወራት ፈጅቶበታል የተባለው ሉምኖስ ፈንድ ጥናት 600 ህጻናትን (ከ7 እስከ 14 ዓመት)፣ 480 መምህራንና 400 ወላጆችን ያካተተ ነው። ጥናቱ የትምህርት ለዓመታት መቋረጥና የጦርነቱ ስነ-ልቦናዊና ማህበራዊ ጫናን ያገናዘበ ስራ መሰራት እንዳለበት ምክረ-ሀሳብ አቅርቧል።
የሉምኖስ ፈንድ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አለማየሁ ኃይሉ (ዶ/ር) በቅድሚያ የቁስለት ህክምና (የትራማ ሂሊንግ) መርሃ-ግብር ሊደረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
“ምንም እንዳልተፈጠረ ከዜሮ ልንጀምር አንችልም። ትምህርት ቢሮ ምንም እንዳልተፈጠረ ነገ ትምህርት እጀምራለሁ ብሎ ልጆቹን ትምህርት አስገብቶ በብላክ ቦርድ ላይ ማስተማር አይችልም። ምክንያቱም መጀመሪያ የቆሰለን ሰው ሳታክሚ ወደ ትምህርት መግባት አይቻልም” ብለዋል።
ስለዚህ “መጀመሪያ ትግራይ ላይ መደረግ ያለበት የትራማ ሂሊንግ ፕሮግራም ሊኖር ይገባል፤ 'ሶሾ ኢሞሽናል ለርኒንግ' በስፋት ሊሰጥ ይገባል፤ ልጆቹ መጀመሪያ መታከም አለባቸው፤ ከታከሙ በኋላ ቀስ በቀስ ወደ ትምህርት ይሄዳል” ሲሉም ተናረግዋል።
ጉዳቱን የሚያካክስ እቅድ ማውጣት እንደሚያስፈልግ ያሰመሩት ኃላፊው፤ ለተማሪዎች የሚሰጠው ትምህርት ተጽዕኖውን ከግምት ውስጥ በማስገባት መነሳት አለበትም ብለዋል።
ይህን ለማድረግ ምን እየሰራ እንደሆነ የጠየቅናቸው የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ጉዳዩ “ዘርፈ ብዙ ስራ፣ ከፍተኛ ገንዘብና እውቀት የሚጠይቅ ውስብስብ ስራ” መሆኑን ገልጸዋል።
“ምንም ነገር በሌለበት ትምህርት ይጀመር ብለን ስናስብ ተማሪዎች ካለባቸው ችግር ቢያንስ ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ እንኳ የሚቀየር ነገር ይኖረዋል በሚል ነው” ብለዋል።
ይህም ከሌሎች ተማሪዎች ጋር፤ ጓደኞቻቸው ጋር ሲገናኙ፤ ለመምህሮቻቸው ጋር ሲገናኙ የራሱ ሆነ ፈውስ ይኖረዋል። ከዚህ እንዲወጡ ስልጠና በጣም አስፈላጊ ነው። ነገር ግን ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ተማሪ ቀላል ቁጥር አይደለም። አነስ ያሉ ሀገራት አጠቃላይ ህዝብ ማለት ነው። ስለዚህ አጠቃላይ እንደ ትግራይ ማገገም ካለብን በስራ ላይ ነው የምናገግመው፤ በስራ ነው የምንድነው የሚል እምነት ነው ያለን” ሲሉም ተናረዋል።
“ለዚህ ነው ትምህርትን ቅድሚያ የሰጠነው” ያት ኃፊው፤ በዚህ ሂደት ግን ስልጠና ደግሞ የራሱ የሆነ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ስለሚኖረው መምህራንን ባገኘነው አጋጣሚና አቅም ላይ በተወሰነ መልኩ ለማሰልጠን ጥረት እናደርጋለን። የሰለጠኑ መምህራን ደግሞ ተማሪዎቻቸውን ሲያስተምሯቸው ከመደበኛ ትምህርት ጋር አዋህደው ይሆናል” ሲሉ አብራርተዋል።
የጉዳቱን ልክና መጠን ሳይታወቅ የሚሰራ ስራ ግን የበለጠ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል ሲሉ አለማየሁ ኃይሉ (ዶ/ር) አሳስበዋል።
ሉምኖስ ፈንድ ሦስት ሚሊዮን ዶላር መድቦ በተመረጡ ወረዳዎች ለተማሪዎችና መምህራን የቁስለት ህክምናን (ትራማ ሂሊንግ) ጨምሮ ወደ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት መመለስ፣ የትምህርት ቤት ምገባና የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ የሚያደርግ ፕሮጀክት እንደሚተገብር ኃላፊው ለአል ዐይን ተናግረዋል።
በትግራይ ባለፈው ሚያዚያ ወር መጨረሻ ትምህርት ሲጀመር ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ተማሪዎች ትምህርት ቤት ይመጣሉ ተብሏል። ሆኖም 500 ሽህ የሚሆኑ ተማሪዎች ብቻ (23 በመቶ) ወደ ትምህርት መመለሳቸውን ኪሮስ ጉዑሽ (ዶ/ር) ገልጸዋል።