በሰላማዊ ሰልፉ በጦርነቱ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ተጠይቋል
በትግራይ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች በርካታ ጥያቄዎች የተስተናገዱበት ሰላማዊ ሰልፍ በዛሬው እለት ተካሂዷል።
ሰላማዊ ሰልፉ መቀሌ፣ አደዋ እና ሽሬ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች በተካሄደው ሰልፍ ላይ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሳተፋቸውን የክልሉ መገናኛ ብዙሃን የዘገቡት።
ሰልፈኞቹ “በወጭ ኃይሎች የተያዙ የትግራይ ክልል መሬቶች ይለቀቁ እና ከተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች ተፈናቅለው በመጠልያ ጣብያዎች ተጠልለዉ የሚገኙ ተፋናቃዮች ቀያቸዉ ይመለሱ” የሚሉ መፈክሮችን አስምተዋል።
በተጨማሪም “ዓለም አቀፍ የተርአዶ ድርጅቶች ብትግራይ ክልል ያቋረጡትን የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲቀጥሉም ሰልፈኞቹ ጠይቀዋል።
የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስ ኤይድ) እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በስርቆት ምክንያት ለትግራይ ክልል የሚሰጡትን የምግብ እርዳታ ማቆማቸውን ከሰሞኑ አስታውቀዋል።
እርምጃውን ተከትሎ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ጌታቸው ረዳ ስርቆቱን የሚያጣራ በሌ/ጄነራል ፍሰሃ ኪዳኑ የሚመራ ኮሚቴ መቋቋሙን ማስታወቃቸው ይታወሳል።
ሰልፈኞቹም የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስ ኤይድ) እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትግራይ ክልል ያቋረጡትን የሰብዓዊ ድጋፍ ዳግም እንዲጀምሩ ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ መንግስት እና በትግራይ ክልል ኃሎች መካከል ባሳለፍነወ ጥቅምት ወር ላይ የሰላም ስምምነት መፈረሙ የሚታወስ ሲሆን፤ ቁልፍ የተባሉ የስምምነቱ ነጥቦች በመተግበር ላይ መሆናቸውን ሁለቱመ ወገኖች መጥቀሳቸው ይታወሳል።
በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ መፍታትን እና በክልሉ የጊዜያዊ አስተዳደርን መመስረትን ጨምሮ መሰረታዊ አገልግሎቶች ወደነበሩበት የመመለስ ስራ መሰራቱም ይታወሳል።