ሚዲያን የማገድ ስልጣን ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ቦርድ እንዲነሳ የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ
በስራ ላይ ያለው አዋጅ ጥፋተኛ ሆነው በተገኙ ሚዲያዎች ላይ አፋጣኝ እርምጃ እንዳይወሰድ አድርጓል ተብሏል
የኢትዮጵያ ብዙሀን መገናኛ ባለስልጣን ሀላፊ ሹመት አሰጣጥ ዙሪያም ማሻሻያ እንዲደረግ ተጠይቋል
ሚዲያን የማገድ ስልጣን ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ቦርድ እንዲነሳ የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ።
በኢትዮጵያ ያሉ ብዙሀን መገናኛዎችን ወይም ሚዲያዎችን በሚመለከት የወጣው አዋጅ ቁጥር 1238/2013 እንዲሻሻል የሚጠይቅ ረቂቅ አዋጅ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲያጸድቀው ቀርቦለታል።
አል ዐይን አማርኛ ይህን ረቂቅ አዋጅ የተመለከተው ሲሆን እንዲሻሻሉ ከተጠየቁ ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ሀላፊነት፣ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አሿሿም፣ የሚዲያዎች ግዴታ እንዲሁም ሚዲያዎች ጥፋተኛ ሆነው ሲገኙ እገዳ ስለሚተላለፍባቸው ሁኔታዎች ዋነኞቹ ናቸው።
በረቂቅ አወጁ ላይ እንዲሻሻል ከቀረቡት ውስጥ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን የስራ አመራር ቦርድ አሰያየም እና አወቃቀር ዋነኛው ነው።
በስራ ላይ ባለው አዋጅ መሰረት ሚዲያዎች የሀገርን ደህንነት ወይም የህዝብን ሰላምና ጸጥታ የሚያደፈርስ ዘገባ ሲሰራጭ በአንቀጽ 81 መሰረት የሚዲያዎችን ፈቃድ የማገድ፣ የመሰረዝና አለማደስ የተመለከተ አስተዳድራዊ ውሳኔ የመስጠት ስልጣን ከቦርዱ ተነስቶ የብዙሀን መገናኛ ባለስልጣን ይሆናል ይላል።
እንደ ረቂቅ ማሻሻያው ሰነድ ከሆነ በስራ ላይ ያለው አዋጅ ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ ሚዲያዎች ወዲያውኑ እና የተፋጠነ እርምጃ እና አውዱን ታሳቢ ያደረገ እርምጃ እንዳይወሰድ ያደርጋል።
እንዲሁም ሚዲያዎች በባለስልጣኑ የተወሰደባቸው ፈቃድ ያለማደስ፣ የገንዘብ ቅጣት፣ ማስጠንቀቂያዎች እና ሌሎች ቅጣቶችን አስመልክቶ ቅሬታቸውን በ14 ቀናት ውስጥ ለቦርዱ የማቅረብ መብትን ሲሰጥ ቦርዱ ደግሞ ለቀረበለት ጥያቄ በ30 ቀናት ውስጥ ምላሽ መስጠት አለበትም ይላል።
ሌላኛው እንዲሻሻል የተጠየቀው ጉዳይ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አሿሿምን በተመለከተ ዳይሬክተሩ በቦርዱ ተመልምሎ በመንግስት አቅራቢነት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሰየማል የሚለው ድንጋጌ ነው።
በረቂቅ ማሻሻያው መሰረትም የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር በጠቅላይ ሚንስትሩ አቅራቢነት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማል ተብሏል።
እንዲሁም በስራ ላይ ባለው መገናኛ ብዙሀን አዋጅ አንቀጽ 55(1) (ረ) መሰረት ከቀጥታ ስርጭት ውጪ በማናቸውም ፕሮግራም ይዘት በሚዲያ ከመሰራጨቱ በፊት ህግን የሚያከብር መሆኑን የማረጋገጥ ግዴታ አለበት የሚለው እንዲሻሻል ተጠይቋል።
ይህ አንቀጽ ሚዲያዎች በቀጥታ ስርጭት ወቅት ህግ ቢጥሱ ተጠያቂ እንዳይሆኑ እክል ፈጥሯል የተባለ ሲሆን ማናቸው የሚዲያ ይዘቶች ከመሰራጨታቸው በፊት ህግን የሚያከብሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ በሚል እንዲስተካከል ተጠይቋል።