ኢትዮጵያ፤ ሩሲያ ኢትዮጵያውያንን ለውጊያ እንደማትመለምል ግልጽ ማድረጓ ተገቢ ነው አለች
ኢምባሲው ሩሲያ ያላት ጦር የምትፈልገውን ለማሳካት በቂ አቅም አለው ብሏል
ዩክሬን ግን ሩሲያ ምልመላ ለማድረግ ጥረት እያደረገች ነው ስትል ትከሳለች
በኢትዮጵያ የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ለወታደርነት ምንም አይነት የምልመላ ጥያቄዎችን እንደማይቀበልና የቬና ኮንቬንሽንን እንደሚያከብር መግለጹ የሚደነቅ መሆኑን ኢትዮጵያ መንግስት አስታውቋል፡፡
ኤምባሲው ትናንት ለአል ዐይን አማርኛ በላከው መግለጫ፤ በፈረንጆቹ በ1961 በቬና የተፈረመውን ኮንቬንሽን እንደሚያከብርና ኢትዮጵያውያንን ለውትድርና እንደማይመለምል ገልጾ ነበር፡፡ ኢምባሲው በርካታ ኢትዮጵያውያን በአካል እና በኢሜል አጋርነት መግለጻቸውን እና ኢምባሲው ይህን እንዲሚያደንቅ ባወጣው መግለጫ መግለጹም ይታወሳል፡፡
ይህ ኮንቬንሽን የውጭ ሀገር ሰዎችን ለወታደራዊ ስራ መመልመል ክልክል መሆኑን ስለሚደነግግ ሩሲያም ይህንን እንደምታከብር ኤምባሲው ገልጾ ነበር፡፡
የሩሲያን ኢምባሲ መግለጫ ተከትሎ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ ኤምባሲው ምልመላ እየተደረገ ነው ለሚሉ ያልተጣሩ መረጃዎች የሰጠው ፈጣንንና ግልጽ ማብራሪያ ኢትዮጵያ የምትቀበለው እንደሆነ ገልጿል፡፡
ሩሲያ የቬናና ኮንቬንሽን እንደምታከብር ማስታወቋ የሚደነቅና ኢትዮጵያ የምትደግፈው እንደሆነም ነው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ያስታወቀው፡፡ ወታደር ለሌላ ሀገር አሳልፎ መስጠት በቬና ኮንቬንሽን ክልክል በመሆኑ የሩሲያ ኤምቫሲ ያለባት ኢትዮጵያም ይህንኑ እንደምታከብር ነው የተገለጸው፡፡
ከሰሞኑ በርካቶች አዲስ አበባ በሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ተሰልፈው መታየታቸው አነጋጋሪ ሆኖ ነበር፡፡ አል ዐይን አማርኛ የሩሲያንም የዩክሬንንም ኤምባሲ የሥራ ኃላፊዎች አነጋግሮ ነበር፡፡ ሩሲያ ያቀደችውን ሁሉ የራሷ ጦር በብቃት እንደሚፈጽመው የገለጸች ሲሆን ፤ ዩክሬን ደግሞ በአዲስ አበባ የሚገነው የሩሲያ ኤምባሲ ምልመላ ለማድረግ ጥረት እያደረገ ነው ብላለች፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስብሰባ ላይ ለሩሲያ ድጋፍ በመስጠቱም ኤምባሲው ምስጋና አቅርቧል፡፡