ኢትዮጵያ ኤምባሲዎቿን ቁጥር የመቀነስ እቅድ አንዳላት አስታወቀች
ኢትዮጵያ ከሏት ከ60 የሚልበጡ ኤምባሲዎች ቢያንስ 30 ያክሉን ልትቀንስ ትችላለች- ጠ/ሚ ዐቢይ
በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራዎችን ለመጠቀምም ታስቧል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ጊዜ እንዳሉት ኢትይጵያ በተለያዩ አገራት የከፈተቻቸውን ኢምባሲዎች የመቀነስ እቅድ አንዳላት ተናግረዋል።
ብዙ አገራት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት እና ወቅቱ ከደረሰበት ቴክኖሎጂ አንጻር ኢምባሲዎቻቸውን እየዘጉ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ ተናግረዋል።
“ከ60 የሚልበጡ ኤምባሲዎች መኖራቸው ለኢትዮጵያ ጠቅሞ እንደ ሆነ መመልከት ያስፈልጋል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢያንስ 30 ኤምባሲ ልትቀንስ እንደምትችል ተናግረዋል።
አንዳንዶቹ ኤምባሲዎች ተዘግተው አምባሳደሮቹ እንደ አስፈላጊነቱ ወደየተሾሙበት ሀገር በቀጠሮ ቢሄዱ ይሻላል ያሉ ሲሆን፤ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራዎችን እንጠቀማለን ሲሉም አክለዋል።
መስከረም 30 ቀን 2014 ዓ.ም የሚመሰረተው መንግስት ይሄንን ከግምት ውስጥ ያስገባ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎችን ያደርጋል ብለዋል።
በአውሮፓ እና አሜሪካ ከተሞች ከአምባሳደሮች በተሻለ መንገድ የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራዎች ስላሉ እነሱን እንጠቀማለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
“ዲፕሎማሲያችን መፈተሽ አለበት” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ከምናወጣው ወጪ እና ከልዩ ልዩ ጉዳዮች አንጻር ቀጣዩ መንግሥት መሰረታዊ የአሠራር ለውጥ ሊያደርግ ያስፈልጋል” ብለዋል።