የግድቡ ተደራዳሪዎች ከ‘ናይል’ ይልቅ ‘ዓባይ’ የሚለውን መጠሪያ እንዲጠቀሙ ተጠየቀ
ስብስቡ ኢትዮጵያ በአባይ ውሃ ላይ ያላትን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚሰራ ማዕከልን ለማቋቋም እንደሚሰራም አስታውቋል
ጥያቄው ስለ አባይ ያገባናል በሚሉ ኢትዮጵያውያን ስብስብ የቀረበ ነው
የግድቡ ተደራዳሪዎች ከ‘ናይል’ ይልቅ ‘ዓባይ’ የሚለውን መጠሪያ እንዲጠቀሙ ተጠየቀ
ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ የድርድር ሂደቶች ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ አንድን የተለየ ሃሳብ የሚያራምድ የኢትዮጵያውያን ስብስብ ብቅ ብሏል፡፡
ስብስቡ በድርድሩ ሂደት ‘ናይል’ በሚል የሚጠቀሰው ውሃ ‘ዓባይ’ በሚል እንዲጠራ ጠይቋል፡፡ ይህንኑ ሃሳቡንም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ ከሰሞኑ አቅርቧል፡፡ አዎንታዊ ምላሽን እንዳገኘም ነው ያስታወቀው፡፡
ስብስቡ ያነሳውን ጥያቄ በተመለከተ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘትም አል ዐይን አማርኛ ከስብስቡ አስተባባሪዎች መካከል አንዱ ከሆኑት ከፖለቲከኛ ግርማ ሰይፉ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
ከአሁን ቀደም ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ የምክር ቤት አባል በመሆን ያገለገሉት አቶ ግርማ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የስራ አስፈጻሚ አባልና የፓርላማ ጉዳዮች ተወካይ በመሆን በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡
ለአቶ ግርማ ምላሽ አብራችሁን ዝለቁ፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡ እንዴት ለምንስ ወንዙ ከናይል ይልቅ ዓባይ መባል አለበት አላችሁ?
አቶ ግርማ ፡ ለምንድነው ያላችሁት ስሙ ዓባይ ስለሆነ ነው ቀላል ነው፡፡ እስከዛሬ ድረስ ኢትዮጵያ ሱዳንና ግብጽ ንግግር እያደረጉ ያሉበት የውሃ ቦታ ዓባይ ነው፡፡ ሲነጋገሩ ግን በሙሉ ናይል እያሉ ነው፡፡ ስለ ዓባይ ጉዳይ፣ ስለ ኢትዮጵያ ውሃ ሃብት እየተነጋገሩ እንደሆነ ያውቃሉ፡፡ ‘ናይል’ በሚባለው ስም ውስጥ ግን ሁሉም የተፋሰሱ ሃገራት አሉበት፡፡
ስለዚህ በዓባይ ጉዳይ የምንነጋገር ከሆነ ስሙን ጠርተን ስንነጋገር ጭንቅላታቸው ውስጥ ‘ክሊክ’ የሚያደርጋቸው ነገር ይኖራል ብለን እናምናለን፡፡ በሰው ቤት ነው እየተነጋገርን ያለነው፡፡ ስለዚህ በትክክለኛ ስሙ መጠራት አለበት፡፡
እኛ ‘ሊትሬቸሮች’ (ድርሳናት) ሁሉ እንዲቀየሩ እንፈልጋለን፡፡ የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎችም አሁን እየተደራደሩበት ያለውን ሰነድ ‘ናይል’ በሚለው ቦታ ላይ ‘ዓባይ’ እያሉ ተክተው ለድርድሩ እንዲያቀርቡ ፍላጎት አለን፡፡ ስለ መርዋን ስለ አስዋን እና ሌሎችም ግድቦች ስናወራ የዛን ጊዜ ‘ናይል’ ማለት እንችላለን፡፡
አል ዐይን፡ ናይልን አናውቀውም ማለት ይህንኑ ዓባይ ይባል የሚለውን ጉዳይ ለማለት ነው ወይስ ምን ለማለት ነው?
አቶ ግርማ፡ ይሄንኑ ለማለት ነው፡፡ በዓለም ላይ ‘ናይል’ የሚባል ወንዝ የለም ለማለት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ‘ናይል’ የሚባል ወንዝ የለም፡፡ አለ…ታውቃለህ? (ሳቅ…)
እስከዛሬ አለማሰባችን ይገርመኛል፡፡ እንዲያውም በጣም ያናድዳል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ናይል የሚሉ ስያሜዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ራሳቸውን ሊጠይቁ ይገባል፡፡ወይ ደግሞ ቢዝነሳቸውን በተፋሰሱ ሙሉ ሃገራት ማድረግ አለባቸው፡፡
ስለዚህ የእኛ ትልቁ ነገር ኢትዮጵያ ‘ዓባይ’ የሚባል ወንዝ ነው ያላት በዚያ ወንዝ ውስጥ የፈለጋትን ማድረግ ትችላለች ነው፡፡
አል ዐይን፡ ‘እኛ’ እያሉ ነው ስብስቡን ወክለው እየተናገሩ ያሉት እናንተ እነማን ናችሁ?
አቶ ግርማ፡ያገባናል የምንል ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ እስከዛሬ ድረስ ባለው ሁኔታ በተናጠል የተለያዩ ባለሙያዎች ምንድነው ማበርከት ያለብን የሚሉ ሰዎች እየተሰባሰቡ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ያደርጉ ነበር፡፡ አሁን ግን ቀጣይነት ያለው ዘላቂ ስራ መሰራት አለበት ብለን ስለምናምን አባይ ተፋሰስ (Abay Basin Center) የሚል ማዕከል አቋቁመን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡
ማዕከሉ በውሃ ጉዳዮች ላይ ምርምሮችን የሚያካሂድ፣ የተካሄዱ ምርምሮችን በተጨባጭ ለህዝብና ለሚዲያ እንዲሁም ለሲቪል ማህበራት የሚያቀርብ፤ ኢትዮጵያ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞቿ የመጠቀም መብት ያላት መሆኑን እንዲያስተምሩ የሚያደርግ ነው፡፡ ማዕከሉን እያቋቋምን ነው፡፡ በዚህ ማዕከል ውስጥ ብዙ ስራዎች ይሰራሉ ብለን እናምናለን፡፡
አል ዐይን፡ እንዴት ባለ መንገድ ነው እነዚህን ስራዎች ለመስራት የታሰበው?
አቶ ግርማ፡ ትልቁ ነገር ከሱዳን እና ከግብጽ ጋር ግብግብ የመግጠም አይደለም፡፡ ትብብርን የማምጣት ነው፡፡ ግብጾች ዓባይ ውሃና አፈር ይዞላቸው ሲወርድ ብቻም ሳይሆን ከውሃው ምርት ጀምሮ ያገባኛል ሊሉ ይገባል፡፡
ለምሳሌ ግብጾች በአካባቢ ጥበቃ ተግባራት ላይ ጉልህና የሚታይ ተሳትፎን እንዲያደርጉ ሃብታቸውን እንዲያፈሱም ጭምር እንፈልጋለን፡፡ ያለበለዚያ ምንም ዓይነት ተሳትፎ በማያደርጉበት ሁኔታ ኢትዮጵያ ከምታጎለብታቸው ምንጮች የሚገኘውን ውሃ እኛ ብቻ እንጠቀማለን ሊሉ አይገባም፡፡ ስለዚህ ውሃውን በማመንጨት ዙሪያም የራሳቸውን ድርሻ እንዲወጡ እንፈልጋለን፡፡
አል ዐይን፡ ስብስቡ ምን ያህል አባላት አሉት በአሁኑ ሰዓትስ ምን እየተሰራ ነው እርስዎስ በስብስቡ ውስጥ ያለዎት የተለየ ሚና አለ?
አቶ ግርማ፡ አባላቱ ብዙ ናቸው፡፡ የተለያዩ ሰዎች የተለያየ ቡድን የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ነው ያለው፡፡ በጉዳዩ ላይ ያገባናል የሚሉ በውጪም በሃገር ውስጥም ያሉ ባለሙያዎች አሉ፡፡
ታስታውስ እንደሆነ የዛሬ 15 ቀን አካባቢ ለእንግሊዝ ኤምባሲ አሰባስበን ያስገባነው ‘ፒቲሽን’ (ፊርማ) አለ፡፡ ፊርማውን ብዙ ሰው ፈርሞታል፡፡ ያ ለእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር (ቦሪስ ጆንሰን) ሄዷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ1929 እና 1959 የሚባሉ ስምምነቶችን በሚመለከት ያለውን የተሳሳተ ተረክ ከእሱም ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያቋርጡ ነግረናቸዋል፡፡ ማድረግ አለማድረጉ የእነሱ ጉዳይ ነው፡፡
አል ዐይን፡ ከሰሞኑ ከተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ ጋር ተወያይታችኋል፡፡ ምንድን ነበር የተወያያችሁት? የእርሳቸውስ ምላሽ ምን ነበረ?
አቶ ግርማ፡ አንደኛ የተከበሩ አፈ ጉባዔው በጥሞና ነው ያዳመጡን፡፡ ማዳመጥ ብቻም ሳይሆን ከአሁን በኋላ የምናደርጋቸውን ነገሮች ግብጽ የምታስቀምጥልንን አጀንዳ ተከትለን ምላሽ የምንሰጥ ብቻ ሳይሆን እኛም አጀንዳ የምንሰጥ የምናስቀምጥ መሆን አለብን፡፡ ስለዚህ ይሄ አንዱ ነው፡፡
በእኛ በኩል ለራሳችን ማድረግ ካለብን አንዱ በጣም ትንሹ ነገር ነው ብለው ነው ቃላቸውን የሰጡን፡፡ ይሄን ለማድረግ የህግ ማዕቀፍ ወይ ሌላ ነገር ምንም ነገር አያስፈልገውም፡፡ ማድረግ ብቻ ነው፡፡ስም ልንተረጉም አንችልም፤ አይጠበቅብንምም፡፡
በመጽሃፍ ቅዱስም ላይ የተቀመጠው ነገር ዓባይ ተብሎ ነው፡፡ በግዕዙም ቢሆን እጅግ አስገራሚ ትርጓሜዎች አሉት፡፡ ‘የከበረ፤ ክቡር’ እንደማለት ነው፡፡ይህን የመሰለ ስያሜ ቀይረህ ‘ናይል’ ማለቱ ተገቢ አይደለም፡፡ እና ያን ክቡር ስም ክብሩን አስጠብቀህ መቀጠል ነው የሚያስፈልገው፡፡ የራሳችንን አጀንዳ የመስጠት ጉዳይ ነው፡፡
አል ዐይን፡ ይህን ማለቱ በድርድሩ ሂደት ላይ ምን ዓይነት አበርክቶ ሊኖረው ይችላል?
አቶ ግርማ፡ ለእኔ በግሌ ብዙ ትርጉም ያለው ድርድር አይደለም፡፡ የፉገራ ድርድር ብዬ ነው የማስበው፡፡ ኢትዮጵያ አትፈልገውም ብዬ ነው የማምነው፡፡ ኢትዮጵያ፣ግብጽና ሱዳን (እ.ኤ.አ በ2010 ወደ ፈረመችው ) ወደ ትብብር ማዕቀፉ መጥተው ስምምነቱን ፈርመው በፍትሃዊነት መጠቀም ስለሚችሉበት ሁኔታ እንዲነጋገሩ ነው የምትፈልገው፡፡ የእኩል ተጠቃሚነት ፍላጎት ነው፡፡ ግብጽ እና ሱዳን ደግሞ የሚፈልጉት ከአሁን ቀደም የነበሩና ታሪካዊ የሚሏቸውን የቅኝ ግዛት የስምምነት ጥቅሞች ማስጠበቅ ነው፡፡ በአጠቃላይ የዓባይን ውሃ ከሌሎች ሃገራት የሚመጣውን የናይል ወንዝ ተጠቅመው መቶ በመቶ ለራሳቸው ተካፍለው ቀሪውን ደግሞ ለበረሃው ሃሩር ሰጥተው ግማሹን ባህር ውስጥ ከተው መኖር ነው የሚፈልጉት እንጂ አሁን ያለው ድርድር የኢትዮጵያ ፍላጎትም አይደለም፡፡ ግን ከጎረቤት ጋራ እውነት እስከያዝን ድረስ ብንነጋገርበት ችግር የለውም፡፡ ለምሳሌ ስለ ግድቡ የግንባታ ሂደትና ደህንነት ብንነጋገርበት ችግር የለውም ማረጋገጫም ለመስጠትም ይቻላል፡፡ ይሄ ስልጡንነት ነው፡፡
አል ዐይን፡ እናመሰግናለን፡፡
አቶ ግርማ፡ እኔም አመሰግናለሁ፡፡