ጠ/ሚ/ር ዐቢይ የግድብ የመጀመሪያ ዓመት የዉሃ ሙሌት በመጠናቀቁ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ
“ለሚከፋፍሉን አካላት ጆሮ ካልሰጠን ከዚህ የላቁ ተግባራትን እንደምናሳካ ግድቡ ማሳያ ነው” ጠ/ሚ/ር ዐቢይ
ግድቡ መሞላቱ ኢትዮጵያ በሁለት እግሯ መቆም እንደምትችል ማሳያ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገልጸዋል
ጠ/ሚ/ር ዐቢይ የግድብ የመጀመሪያ ዓመት የዉሃ ሙሌት በመጠናቀቁ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ
የግድቡ የመጀመሪያ ዓመት ሙሌት መጠናቀቁን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
“ግድባችን መሞላቱ ከእንግዲህ በሁለት እግራችን መቆም እንደምንችል የዓለም ህዝብ እንዲያውቅ የሚያደርግ ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
“ማንንም ሳናስቸግር እና ሳንጎዳ የመጀመሪያውን ዓመት የዉሀ ሙሌት አሳክተናል ፤ የግድቡ ዉሀ ሞልቶ መፍሰስ ጀምሯል”ም ብለዋል፡፡
የግድቡ ዉሀ ሞልቶ መፍሰሱን የሚያሳይ የኢዜአ ቪዲዮም በኢቲቪ ተላልፏል፡፡
“እንኳን ጉዳት ይቅር እና ግድቡ ለታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ጥቅም የሚያስገኝ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሱዳን እና ግብጽ የሚያገኙት የዉሃ መጠን ሳይቀንስ የግድቡን የዉሃ ሙሌት ማከናወናችን ለዚህ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይነትም ኢትዮጵያ ሱዳንን እና ግብጽን የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት ፣ ይልቁንም የሚጠቀሙበትን ዕድል እንደምትፈጥር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
የህዳሴ ግድቡን ግንባታ ያስጀመሩ የቀድሞዎቹን ጠቅላይ ሚኒስትሮች ጨምሮ ያስተዳደሩ ፣ የሰሩ፣ የተደራደሩ እና የተለያዩ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላትንም አመስግነዋል፡፡
“የግድቡን ግንባታ እና ቀሪ የዲፕሎማሲ ጉዳዮችን ማጠናቀቅ ይጠበቅብናል” ያሉም ሲሆን ህብረተሰቡ ለግንባታው በተለያየ መልኩ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
በቀጣዩ ዓመት የግድቡ ሁለት ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምሩ የሚጠበቅ ሲሆን “በ2015 ዓ.ም ግድቡ በሙሉ አቅሙ ኃይል የማመንጨት ደረጃ ላይ ይደርሳል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
“ለሚከፋፍሉን እና ለሚያባሉን አካላት ጆሮ ካልሰጠን” ከዚህ የላቁ ተግባራትን ማከናወን እንደምንችል ግድቡ ማሳያ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ግድቡ በደለል እንዳይሞላ ኢትዮጵያውያን የጀመሩትን ችግኝ የመትከል የአረንጓዴ አሻራ ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የህዳሴው ቤተሰብ በቀጣይ ለግድቡ ድጋፉን በመቀጠል ፣ አረንጓዴ አሻራውን ማሳረፍ እና ራሱን ከኮሮና ወረርሽኝ በመጠበቅ የክረምቱን ምቹ ወቅት በመጠቀም የግብርና ስራውን በንቃት ማከናወን እንዳለበት እና በሌሎችም ስራዎች ጥንቃቄ ሳያጓድል ተግባሩን እንዲያከናውን ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ግድቡ እስካሁን ከመሬት በላይ 60 ሜትር የተገነባ ሲሆን ከ 140 ሜ. እስከ 170 ሜትር ከፍታ የግድቡ ግንባታ ይቀጥላል፡፡