የሽብር ተግባር ሊፈጽሙ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለፀ
ለሽብር ተግባር ማስፈጸሚያ ሊውል የነበረ ከ305 ሺህ በላይ ዶላር እና ከ2 ሚሊየን በላይ ብር መያዙ ተገልጿል
በሀገር ውስጥ እስካሁን የቡድኑን የከተማ ህዋስ አባላት ጨምሮ 71 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል
በአዲስ አበባና በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች የተቀናጀ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም አቅደው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡
የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ በውጭ እና በውስጥ ፀረ-ሰላም ኃይሎች የሚደገፉ የሸብርተኞቹ የህወሓትና የሸኔ ቡድን አባላት በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ በዝግጅት ላይ እንዳሉ በተደረገባቸው የተቀናጀ ክትትል በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ይህን እኩይ የጥፋት ሴራ ለመፈጸም ከውጭ በተለያዩ አካላት በሚደረግላቸው የገንዘብና የሎጅስቲክስ ድጋፎች ተልዕኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት የሸብርተኞቹ የህወሓትና የሸኔ ቡድን አባላት ከከባድ እስከ ቀላል የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎችን ከመሰል ጥይቶች፣ ቦምቦችና ተቀጣጣይ ቁሶች ጋር ለጥቃት ሊጠቀሙባቸው ያዘጋጇቸው ቢሆንም፤ የታቀደውን የጥፋት ተልዕኮ ማክሸፍ መቻሉን መግለጫው አትቷል።
መግለጫው አክሎም በተደረገ ጥብቅ ክትትልና ፍተሻ ለጥፋት ተልዕኮ መፈፀሚያቸው ሊጠቀሙበት የነበረ ከ305 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር እና ከ2 ሚሊየን በላይ የኢትዮጵያ ብር መያዙን አስታውቋል፡፡
ለእነዚህ የሽብር ቡድኖች የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን፣ ቦምቦችን፣ ለፍንዳታ የሚውሉ ተቀጣጣይ ቁሶችን እንዲሁም ሰነዶችን በስውር ለመስጠት ሲያጓጉዙ የነበሩ በርካታ የቡድኑ ተጠርጣሪ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጋራ ግብረ ኃይሉ በመግለጫው አመላክቷል፡፡
ከተጠርጣሪዎች መካከልም አብዲሣ ጣፋ ቆጮልቴ እና ኤብሣ ተረፋ ቶኮሣ የተባሉት ግለሰቦች ከአማራ ክልል ሁመራ አካባቢ በኮድ ሁለት የታርጋ ቁጥር A70977-አ.አ ሚኒባስ መኪና የውስጥ አካል የተለያዩ የጦር መሳሪዎችንና ጥይቶችን ሰግስገውና ደብቀው መዳረሻቸውን ምዕራብ ኦሮሚያ አድርገው በደሴ በኩል አዲስ አበባ ሊገቡ ሲሉ ለገጣፎ ላይ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጿል።
በተመሳሳይ አርጆ አለማየሁ ዋቆ የተባለች የሸኔ ቡድን አባል ሶላር የተገጠመላቸው ዓለም አቀፍ የሳተላይት ስልኮችን በሞያሌ በኩል በማስገባት ወደ ተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በድብቅ ለማሰራጨት ስትሞከር ቡራዩ ከታ ላይ በቁጥጥር ስር መዋሏን የጋራ ግብረ ኃይሉ ስታውቋል።
ራቢራ ዊርቱ ሞሲሳ፣ ደረጄ ዱጋሳ ሆርዶፋ እና ወንደሰን መግራ ታደሰ የተባሉ ሌሎች የሽብር ቡድኑ አባላትም ተጨማሪ የሳተላይት ስልኮችን ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ ለማስገባት ሲሞክሩ በነበረው ሚስጥራዊ ክትትል በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቅሷል።
ሸብርተኛው የሸኔ ቡድን በተደራጀና በተጠና መንገድ ግድያ እንዲፈፅሙ አዲስ አበባና በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች ያሰማራቸው የአባ ቶርቤ ቡድን አባላት ተመሳስለው ጥቃት የሚፈፅሙባቸው የመከላከያ ሰራዊት የቀድሞ ደንብ ልብሶችንና እና የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ጭምር በድብቅ ሲጓጓዙ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መግለጫው አትቷል።
አበራ ሙለታ፣ ለሊሳ አዳሙ፣ አበራ ጌታ፣ ሙሌ ስዩሜ እና አብርሃም አቡ የተባሉ የቡድኑ አባሎችና የድርጊቱ ተዋናዮች እንዲሁም አሽከርካሪውና ረዳቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መግለጫውም ጠቁሟል፡፡
የሽብር ቡድኑ በጅማ ከተማ ጥቃት ለመፈጸም ስምሪት የሰጣቸው ኢያሱ ለማ፣ ካሊድ ሰይድ፣ አብደላ አባ በላይ፣ ሰይፉ በላይ እና ነጋሳ ኬኔሳ የተባሉ ተጠርጣሪዎችም ከታጠቋቸው የእጅ ቦምቦችና እና ሽጉጦች እንዲሁም ከሌሎች የጥፋት ተልዕኮ መፈጸሚያ ቁሶች ጋር መያዛቸውንም ነው ያመላከተው፡፡
በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚኖሩና ለአሸባሪው የሸኔ ቡድን የገንዘብና የሎጅስቲክስ ድጋፎች የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ያመላከተው መግለጫው፤ እነርሱም ጀምበሩና አበበ አሜሪካ፤ ገመቹ፣ አብደላ እና ተርፋ አውስትራሊያ ዱጋሳ ኖርዌይ እንዲሁም ቶለሺ ታምሩ ወይም ገቢሴ፣ ገመቹ አቦዬ፣ ለማ ረጋሳ ወይም ቢቂላ እና ጃራ ቱለማ ኬንያ እንደሚኖሩም አውስቷል፡፡
እነዚህን የሽብር ቡድኑን እንቅስቃሴ እየደገፉ ያሉትን በድምሩ 15 ተጠርጣሪዎችን ማንነት በማጣራትም ለህግ ለማቅረብ ከወዳጅ ሀገራት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጾ፤ በሀገር ውስጥ እስካሁን የቡድኑን የሽብር እንቅስቃሴ ለመግታት በተወሰደው እርምጃ የቡድኑን የከተማ ህዋስ አባላትን ጨምሮ 71 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ብሏል፡፡
መግለጫው አያይዞም ለሽብር ቡድኑ የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ የ80 ተጠርጣሪ ግለሰቦች የገንዘብ ስርዓት እንዲቋረጥ የተደረገ መሆኑን እያሳወቀ፥ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የቡድኑ ዋና ዋና የገንዘብ አስተላላፊ ተብለው የተጠረጠሩ 6 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል፡፡
ሌሎችንም በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን አመላክቷል፡፡
መግለጫው አክሎም የሽብርተኛው የሕወሓት ቡድን በመንግስት የተወሰደበትን ተከታታይ እርምጃ መቋቋም ባለመቻሉ “ክብሪት” የሚል መጠሪያ የሰጠውን ገዳይ ቡድን በክልሉ ዋና ዋና ከተሞችና በአዲስ አበባም ጭምር ለማሰማራት መሞከሩንም አትቷል፡፡
በአሜሪካ የሚኖሩ ጀኔራል ፍስሃ ማንጁስ ካህሳይና ወዲ ምጉላት የተባሉ ግለሰቦች በሆላንድ የሚኖሩ ተክላይ እና አታክልቲ፣ እንግሊዝ የሚኖረው ታከለ፣ ስዊድንና ደቡብ ሱዳን የሚኖሩት ተስፋይ ንጉስና ሰይፈ አምባዬ የተባሉ ተጠርጣሪዎች ሽብርተኛውን የሕወሓት ቡድን በገንዘብ የሚደግፉ መሆናቸው በማስረጃ የተረጋገጠ መሆኑን በመግለጽ የጋራ ግብረ ኃይሉ ግለሰቦቹን በህግ ተጠያቂ የማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ነው ያስታወቀው፡፡
በሀገር ውስጥ ሆነው ለቡድኑ የገንዘብና የሎጅስቲክስ ድጋፎችን ሲያደርጉ የነበሩ 32 የቡድኑ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም እና በቡድኑ ለሽብር ድርጊቱ ሊውሉ የነበሩ የቡድንና የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎች፣ የሬዲዮ መገናኛዎች እና ሌሎች ተቀጣጣይ ቁሶችም መያዛቸውን ጠቁሟል፡፡