የመከላከያ ሰራዊት ሽሬ፣ አላማጣና ኮረም ከተሞችን መቆጣጠሩን መንግስት አስታወቀ
የመከላከያ ሰራዊት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች የሰባዓዊ አገልግሎቶችን ለማስቀጠል ዝግጅት እየተደረገ ነው
ህወሓት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትና አጋር ኃይሎች በትናንትናው እለት የሽሬ ከተማን መያዛቸውን አስታውቋል
የመከላከያ ሰራዊት ሽሬ፣ አላማጣ እና ኮረም ከተሞችን መቆጣጠሩን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በትግራይ ክልል የሚገኙ ከተሞችን መቆጣጠሩን አስታውቋል።
በዚህም የመከላከያ ሰራዊት የሰቪል ዜጎችን ደህንነት በጠበቀ መልኩ ያለከተማ ውጊያ ሽሬ፣ አላማጣ እና ኮረም ከተሞችን መቆጣጠሩን ባወጣው መግለጫው አረጋግጧል።
የኢትዮጵ መንግስት መከላከያ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ከሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ተቋማት ጋር በመሆን የሽሬ አውሮፕላን ማረፊያን ጭምር በመጠቀም የድጋፍ አገልግሎቶችን ለማስጀመር ተገቢውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም በመግለጫው ተመላቷል።
በተጨማሪም መንግስት ከሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ተቋማት ጋር በመሆን ተጨማሪ ድጋፍ የሚደርሱባቸውን አመራጮች እያስተባበረ መሆኑን እና በሰሜን ጎንደር በኩል ወደ ሽሬ እንዲሁም በኮምቦልቻ፣ ደሴ፣ ወልዲያ፣ ቆቦ፣ አላማጣ የድጋፍ መስመሮችን እያመቻቸ መሆኑን አስታውቋል።
መንግስተ ከሰብአዊ ድጋፍ በተጨማሪም የተቋረጡ አገልግሎቶችን ለማስመጀመር የሚያስችሉ ቴክኒካል ድፎጋችን እንደሚያመቻችም በመግለጫው አስታውቋል።
ህወሓት ትናንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትና አጋር ኃይሎች የሽሬ ከተማን ጥቅምት 7፣ 2015 ዓ.ም መያዛቸውን አስታውቆ ነበር።
የኢትዮጵያ መንግስት በትናትናው እለት ባወጣው መግለጫ በትግራይ ክልል የሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎችንና የፈዴራል ተቋማትን እንደሚቆጣጠር ማስታወቁ አይዘነጋም።
በመግለጫውም ለሶስተኛ ዙር በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ግጭት ህወሓት ነሀሴ 18 2014 ዓ.ም በከፈተው ጥቃት መካሄድ እንደጀመረ አስታውቋል።
ህወሓት ሶስተኛ ዙር ጦርነትን የከፈተው የፌደራል መንግስት በአፍሪካ ህብረት ስር በሚካሄድ ድርድር ላይ ያለ ቅድመ ሁኔታ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን ማሳወቁን ተከትሎ ነው ያለው መግለጫው፤ አሁን እየተካሄደ ላለው ግጭትም ዋነኛው ተጠያቂ ህወሓት ነው ብሏል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት ባሳለፍነው እሁድ ባወጡት መግለጫ ባወጡት መግለጫ ተፋላሚ ኃይሎች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም እና የሰብዓዊ አገልግሎቶች ወደ ነበሩበት አንዲመለሱም ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።