መንግስት “በትግራይ ክልል የሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎችንና የፈዴራል ተቋማትን እቆጣጠራለሁ” አለ
መንግስት በአፍሪካ ህብረት ስር ለሚካሄደው የሰላም ድርድር መሳካት ቁርጠኛ መሆኑን ገለፀ
ህወሓት ከውጭ ኃይሎች ጋር በመሆን የሀገሪቱን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የጣለ መሆኑን መንግስት አስታውቋል
የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል የሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎችንና የፈዴራል ተቋማትን እንደሚቆጣጠር አስታወቀ።
የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገለግሎት በዛሬው እለት በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት እንዲሁም በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ስለሚካሄደው ድርድር አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫውም ለሶስተኛ ዙር በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ግጭት ህወሓት ነሀሴ 18 2014 ዓ.ም በከፈተው ጥቃት መካሄድ እንደጀመረ አስታውቋል።
ህወሓት ሶስተኛ ዙር ጦርነትን የከፈተው የፌደራል መንግስት በአፍሪካ ህብረት ስር በሚካሄድ ድርድር ላይ ያለ ቅድመ ሁኔታ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን ማሳወቁን ተከትሎ ነው ያለው መግለጫው፤ አሁን እየተካሄደ ላለው ግጭትም ዋነኛው ተጠያቂ ህወሓት ነው ብሏል።
“ህወሓት እያካሄደ ያለው መጠነ ሰፊ ጥቃት ላይ የውጭ ተዋናዮች በተደጋጋሚ እና አደገኛ በሆነ መልኩ የኢትዮጵያን አየር ክልል እየጣሱ ነው” ያለው መንግስት፤ ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ መንግስት የሀገርን ሉአላዊነት እና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ እርምጃ ወደ መውሰድ መግባቱን በመግለጫው።
የኢትዮጵያ መንግስት የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት እንድነት ለማስጠበቅ ሲል በትግራይ ክልል የሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎችንና በክልሉ የሚገኙ የፈዴራል መንግስት ተቋማትን እንደሚቆጣጠርም በመግለጫው አስታውቋል።
መንግስት ይህንን እርምጃ ለመውሰድ የተገደደው በህወሓት ኃይል ተደጋጋሚ ጥቃት ብቻ ሳይሆን ይህ ኃይል ከውጭ ኃይሎች ጋር በመሆን የአገሪቱን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የጣለ በመሆኑ እንደሆነ የመንግስት ኮሚንኬሼን አገልግሎት በመግለጫው አመልክቷል።
እርምጃው የኢትዮጵያን የአየር ክልል ማስከበርና የአገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት እንድነት አደጋ ላይ እንዳይወደቅ ከማድረግ በተጨማሪ ለትግራይ ክልል ህዝብ አስፈላጊው የሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲደርስም ጠቃሚ መሆኑን ገልጿል።
ውጊያው ላይ የመከላከያ ሰራዊት ዓለም አቀፍ የሰባዓዊ ህጎችን አክብሮ እንደሚንቀሳቀስ ያስታወቀው መንግሰት፤ በንጹሃን ላይ የሚደርስ ጉዳትን ለመቀነስ የመከላከያ ሰራዊት በከተሞች አካባቢ የውጊያ ኦፕሬሽኖችን በተቻለ አቅም እንደማያካሂዱ አስታውቋል
የኢትዮጵያ መንግስት ሰባዓዊ አገልግሎቶች ተደራሽ እንዲሆኑ ከዓለም አቀፍ የሰባዓዊ ተቋማት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ያስታወቀ ሲሆን፤ ሲቪል ዜጎች እና የሰብዓዊ ተቋማት ሰራተኞች ራሳቸውን ከህወሓት ወታደራዊ ተቋማት እንዲያርቁም አሳስቧል።
መግለጫው አክሎም መንግስት በአፍሪካ ህብረት ስር የሚካሄደው የሰላም ድርድር ውጤታማ እንዲሆን ቁርጠኛ መሆኑን በመግለጫው አስታውቋል።
ቀጣይነት ያለው ሰላም አንዲመጣ አጠቃላይ እና በድርድር ላይ በተመሰረት መልኩ ችግሮች መፈታት እንዳለባቸው እንደሚያምንም መንግስት በመግለጫው አስታውቋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት በትናንትናው እለት ባወጡት መግለጫ ተፋላሚ ኃይሎች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም እና የሰብዓዊ አገልግሎቶች ወደ ነበሩበት አንዲመለሱም ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ህወሓት ይህንን ተከትሎ ባወጣው መጠው መግለጫ “አስቸኳይ የቶክስ አቁም ጥሪ ለማክበር ዝግጁ ነን”ብሏል።
ከሁለት ሳምንታት በፊት በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት በደቡብ አፍሪካ ሊካሄድ ታስቦ የነበረው የሰላም ንግግር ላይ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቦ፣ ሁለቱም ወገኖች ተሳታፊ ለመሆን ፈቃደኛ ገልጸው ነበር።
ነገርግን ሊካሄድ የታሰበው ድርድር በሎጂስቲክስ ምክንያት መራዘሙ ይታወሳል።