የተመድ ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ “በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ ነው” አሉ
የተመድ ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ “በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ ነው” አሉ
የተመድ ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ “በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ ነው” አሉ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ “በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ ነው” አሉ።
ዋና ጻሃፊው ኢትዮጵያን በተመለከተ ትናንት ምሽት በሰጡት መግለጫ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እጅጉን እንዳስጨነቃቸው ተናግረዋል።
“አሁን በኢትዮጵያ ባለው ሁኔታ ማህበራዊ ትስስር እየተበጣጠሰ ነው” ያሉት ጸሃፊው፤ “የሲቪሎች ህይወት እየቀጠፈና ውድመት እያስከተለ ያለው ጦርነት ማብቃት አለበት” ሲሉ አሳስበዋል።
ጉቴሬዝ “የኤርትራ ኃይሎች ከኢትዮጵያ መውጣታቸውን ጨምሮ በትግራይ ክልል ያለው ግጭት አሁኑኑ ማብቃት አለበት” ብለዋል።
አሁን በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ወታደራዊ መፍትሄ የለውም ሲሉም ተናግረዋል።
ዋና ጸሃፊው ጦርነት እንዲያበቃ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ህብረት ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑ በድጋሚ ያረጋገጡ ሲሆን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሁን ለሰላም መሰባሰብ አለበት ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
የአፍሪካ ህብረት፣ አውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ ትናንት ባወጡት መግለጫ ሁሉም ተፋላሚ ኃይሎች እየተባበሰ የመጠውን ጦርነት እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት እሁድ እለት ባወጡት መግለጫ " መንግስት እና ህወሓት በአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ በሚመራው እና በዓለም አቀፉ መህበረሰብ በሚደገፈው በደቡብ አፍሪካ ወደ ተጠራው የሰላም ድርድር ሊመጡ ይገባል" ሲሉ አሳስበዋል።
ህወሓት በዓለም አቀፍ ደረጃ ድጋፍ ያገኘ የተኩስ አቁም ጥሪ እንደሚያከብር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በትናትናው እለት ባወጣው መግለጫ ለሰላም ቁርጠኛ መሆኑን ገልጾ በሰሜን ኢትዮጵያ የመከላከል እርምጃ እየወሰድኩ ያለሁት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማረጋገጥ በማስፈለጉ ነው እንደሆነ አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትና አጋር ኃይሎች የሽሬ ከተማን መያዛቸውን ህወሓት ገልጿል።
ህወሓት ትናንት ማምሻውን ባወጣው እና በክልሉ መገናኛ ብዙሃን በተላለፈው መግለጫ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትና አጋር ኃይሎች የሽሬ ከተማን ጥቅምት 7፣ 2015 ዓ.ም መያዛቸውን አስታውቋል።
የሽሬ መያዝን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል እስካሁን በይፋ የተባለ ነገር የለም።
ከሁለት ሳምንታት በፊት በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት በደቡብ አፍሪካ ሊካሄድ ታስቦ የነበረው የሰላም ንግግር ላይ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቦ፣ ሁለቱም ወገኖች ተሳታፊ ለመሆን ፈቃደኛ ገልጸው ነበር፡፡
ነገር ግን ሊካሄድ የታሰበው ድርድር በሎጂስቲክስ ምክንያት መራዘሙ ይታወሳል፡፡