የሰራዊቱን መለዮ ለብሰው በአምልኮ ስፍራዎች በሚገኙ የመከላከያ አባላት ላይ እርምጃ ይወሰዳል ተባለ
የእምነት ተቋማቱ ለምን መከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ክትትል እንደሚያደርግም ነው መከላከያ ያስታወቀው
ከሰሞኑ የሰራዊቱን መለዮ ለብሰው ሲያመልኩ በነበሩ የመከላከያ አባላት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድም ተገልጿል
የሰራዊቱን መለዮ ለብሰው በሐይማኖት እና ማምለኪያ ስፍራዎች በሚገኙ አባላቱ ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሰራዊት አስታወቀ፡፡
መከላከያ አባሎቹ መለዮ ለብሰው በሐይማኖት ማምለኪያ ስፍራዎች እንዳይገኙም ከልክሏል፡፡
የእምነት ተቋማቱ ለምን መከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ክትትል እንደሚያደርግም ነው ያስታወቀው።
የአገር መከላከያ ሰራዊት ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ በጉዳዩ ዙሪያ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።
ዳይሬክተሩ በመግለጫቸው “ሠራዊቱ ገለልተኛ ፣ ዩኒፎርምም ሆነ ሀይማኖት የሌለው” መሆኑን ገልጸዋል፡፡
መከላከያ ሠራዊት ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ የማይወግን እና የማንኛውንም ዕምነት የማያራምድ መሆኑ በህገ- መንግስቱም ይሁን በቅርቡ በጸደቀው የመከላከያ ስትራቴጂክ የግንባታ ሰነድና በአስተዳደራዊ ደንቡ ላይ በግልጽ ተደንግጓልም ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡
ይሁን እንጂ በቅርቡ የመከላከያ ሠራዊት ዩኒፎርም በመልበስ በተለያዩ የዕምነት ተቋማት ሲያመልኩ የሚያሳይ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ ፡፡
ይህ ድርጊት በሚመለከታቸው የተቋሙ የፍትህ አካላት ተጣርቶ ርምጃ እንደሚወሰድ አረጋግጠዋል፡፡
ከዚህ በፊት የመከላከያን የደንብ ልብስ በመልበስ በተለያየ የዕምነት ተቋም ሲያመልኩ የተገኙ በቁጥጥር ስር ውለው እና ማገገሚያ ማዕከል ገብተው ቅጣታቸውን ፈጽመው የወጡ ሰዎች መኖራቸውን ያስታወሱት ኮ/ል ጌትነት፣ መሰል ድርጊቶችም በሰራዊቱ ውስጥ ሲከሰቱ የተለያዩ አስተዳደራዊ ርምጃዎች ተወስደዋል ብለዋል።
የመከላከያ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ እንዳሉት፣ በቅርቡ በተለያዩ የዕምነት ተቋማት የጀግናውን እና የየትኛውንም እምነት የማይወክለውን የሠራዊቱን የደንብ ልብስ በመልበስ የታዩ ግለሰቦችን በማጣራት ክስ እንደሚመሰረትባቸው ገልጸዋል።
በእንደዚህ አይነት ጥፋት የሚገኙ የሰራዊት አባላት እስከ 5 አመት እንደሚያሳስርም ገልፀዋል።
በዚህ ድርጊት የተሳተፉ አባላት “እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ርምጃም ይወሰድባቸዋል- ዩኒፎርሙ ዕምነትም ሆነ ሀይማኖት የለውምና” ሲሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
የመከላከያ ሰራዊት አባላት የፈለጉትን ዕምነት የመከተል መብት ቢኖራቸውም “የተቋሙን መለዮ ወይም የደንብ ልብስ በመልበስ ማምለክ የተከለከለ” መሆኑንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል ፡፡
የዕምነት ተቋማቱም በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት በርካታ ሙያዎች ውስጥ “ሠራዊቱን መርጠው በዚህ መልኩ ማሳየት የፈለጉበት ምክንያት ምን እንደሆነ” መከላከያ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚከታተለው አሳስበዋል ፡፡
በተጨማሪም በአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያ፣ የተቋማችን ዩኒፎርም የለበሱ እና በፓትሮል መኪና ሆነው ሰው እየደበደቡ የተላለፈው ዘገባ እውነተኛነቱ ተረጋግጦ እርምጃ እንደሚወሰድ ሚኒስቴሩ በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።