ሶስት የአልሸባብ ቡድን አመራሮችን መግደሉን የኢትዮጵያ መከላከያ አስታወቀ
ከተገደሉት የአልሸባብ አመራሮች መካከል የፕሮፓጋንዳ ኃላፊው ፉአድ መሀመድ ከኬፍ ይገኝበታል ብሏል መከላከያ
መከላከያ አልሸባብ ኢትዮጵያን ለማጥቃት ያዘጋጃቸውን የትጥቅና ስንቅ ዴፖዎች ማውደሙን ገልጿል
የአልሻባብ ቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳ ኃላፊን ፉአድ መሐመድ ከሌፍ (ሼንጎሌ) ጨምሮ ሶስት የአልሸባብ አመራሮችን መግደሉን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አስታወቀ።
የመከላከያ ኃይል ስምሪት ኃላፊና ጊዜያዊ የፀጥታ ኮማንድፖስት አስተባባሪ ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው ለኢዜአ እንደተናገሩት የአልሻባብ ቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳ ኃላፊን ፏአድ መሐመድ ከሌፍ (ሼንጎሌ) ጨምሮ ሶስት የቡድኑ አመራሮች ተገድለዋል፡፡
- አቶ ሙስጠፌ፤ “ሁልሁል ኦፕሬሽን” አልሸባብን የደመሰሰውን የክልሉን ልዩ ሃይል ለአዲስ ተልዕኮ ወደ ድንበር ሸኙ
- ድንበር ጥሰው የገቡ ከ209 በላይ የአልሸባብ ታጣቂዎች መደምሰሳቸውን የኢትዮጵያ መንግስት አስታወቀ
ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ ባለፉት ቀናት ከኢትዮጵያ አየር ኃይል ጋር በቅንጅት በተወሰደ ርምጃ የሽብር ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማጥቃት ያዘጋጃቸውን የትጥቅና ስንቅ ዴፖዎች ማውደም ተችሏል ብለዋል፡፡ ጄነረሉ ከአልሸባብ አመራሮች በተጨማሪ የቡድኑ ታጣቂዎች መገደላቸውን አስታውቀዋል፡፡
መከላከያ ደመሰሰኳቸው ያላቸው የአልሸባብ አመራሮች የተዘረዘሩት ናቸው፡፡
1. ፉአድ መሐመድ ከለፍ (ሼንጎሌ) የአልሸባብ ቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳ ሃላፊ፣
2.አብዱላዚዝ አቡ ሙሳ የአልሸባብ ቃል አቀባይ፣
3.ኡቤዳ ኑር ኢሴ የአልሸባብ የቦኮል ዞንና የኢትዮጵያ ድንበሮች አዋሳኝ ሃላፊ
ባለፈው ሳምንት "አቶ" በሚባል ቦታ ወደ ሶማሌ ክልል አፍዴር ዞን የገባ የአልሸባብ ታጣቂ ቡድን መደምሰሱን የክልሉ ፀጥታ ምክር ቤት ቅዳሜ እለት ማስታወቁ ይታወሳል።
የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው የገቡ ከ209 በላይ የአልሸባብ ታጣቂዎች መደምሰሳቸውን የኢትዮጵያ መንግስት አስታውቆ ነበር።